ኢራን ከአሜሪካ ጋር ድርድር እያደረገች አለመሆኑን አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, IRIB
የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አገራቸው ከአሜሪካ ጋር መልዕክቶችን መለዋወጧን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት መደበኛ የሆነ ድርድር እየተደረገ አለመሆኑን ገለጹ።
ኢስማኤል ባጋይ ቴህራን አሁን ቅድሚያ የምትሰጠው ሉዓላዊነቷን መከላከል፣ የግዛት አንድነቷን ማስጠበቅ እና ለሕዝቧ መብት መሆኑን ገልጸው ወደ ድርድር ፈጥነው እንደማይገቡ ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ ዋሺንግተን ዲፕሎማሲን በወታደራዊ እርምጃ ውድቅ ታደርጋለች ሲሉ የኮነኑ ሲሆን አሜሪካ ወደ ድርድር ለመመለስ ያለውን ሁኔታ አበላሽታዋለች ብለዋል።
ባጋይ ከአውስትራሊያው ኦአርኤፍ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “መልዕክቶችን እየተለዋወጥን ነው፤ ነገር ግን አሁን ቅድሚያ የምንሰጠው ለኢራን ሉዓላዊነት፣ ለግዛት አንድነት እና ለሕዝቧ መብት መከበር ነው” ብለዋል።
የቃል አቀባዩ አስተያየት ምንም እንኳ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል መደበኛ ድርድር ባይጀመርም ቀጥተኛ ያልሆነ ግንኙነት እየተካሄደ መሆኑን ይጠቁማል።
ከዚህ ቀደም ቀጣናዊ አደራዳሪዎች ፓኪስታን እና ኳታር በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የመልዕክት ልውውጥ በማቀላጠፍ ረገድ ሚና ነበራቸው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዩ አስተያየት የተሰማው አሜሪካ ለሁለት ሳምንት ስታካሄድ የነበረውን ጥቃት ማቆሟን ከገለጸች በኋላ ነው።
የጥቃቶቹ መቆም ዳግም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሊጀመር ይችላል የሚል ተስፋ አጭሯል።
በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን የነዳጅ አቅርቦት አስተጓጉሏል።





