ኤአይ 'በረከት ወይስ መርገምት?' እንዴት እንጠቀመው? ኢትዮጵያዊው የማይክሮሶፍት ባለሙያ ምን ይመክራል?

ሰው ሠራሽ አስተውሎት በሁለት ተቃራኒ ምልከታዎች እየተጎተተ ይመስላል።
ሥራችንን ይቀማናል፣ በስተመጨረሻም ያጠፋናል የሚል ፍርሃት በአንድ ወገን፤ ለሁሉም ችግሮቻችን መፍትሔ የሚሰጥ መሣሪያ ነው የሚለው ፍፁም እምነት ደግሞ በሌላኛው ጽንፍ።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) በሰው ልጆች የሥልጣኔ ታሪክ ጉልህ ከሆኑ ክስተቶች በዋናነት ይጠቀሳል።
ዓለማችንን በማይታመን ፍጥነት እየለወጠ ያለውን ሰው ሠራሽ አስተውሎት በአግባቡ መገንዘብ ምርጫ ሳይሆን ግዴታ እየሆነ የመጣም ይመስላል።
ስለዚህም ስለ ሰው ሠራሽ አስተውሎት የተዛቡ ምልከታዎች ምንድን ናቸው? በቴክኖሎጂው ውስጥ አፍሪካ ያላት ቦታ ምን ይመስላል? ለወደፊቱ የኤአይ ዓለም እንዴት መዘጋጀት እንችላለን? የሚሉና ተያያዥ ጥያቄዎችን አንስተን ባለሙያ አነጋግረናል።
ዶ/ር ግርማው አበበ ታደሰ ይባላል። በማይክሮሶፍት፣ የኤአይ ፎር ጉድ ላብ የአፍሪካ መሪ ሲሆን፤ የተባበሩት መንግሥታት ያቋቋመው የሰው ሠራሽ አስተውሎት የዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ፓናል አባልም ነው።
አባቱ መምህር መሆናቸው ትምህርት ወዳድ እንዳደረገው ይናገራል።
ልጅ ሳለ ነገሮች እንዴት ይሠራሉ? የሚለውን ለማወቅ እንደሚጓጓ ያስታውሳል። እናም ሒሳብ እና ሳይንስ ይወዳል።
አርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ኤሌክትሪካል ምህንድስና አጥንቷል። በጣሊያን፣ ፖርቹጋል፣ ቤልጅየም፣ ስፔን እና እንግሊዝ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪውን ተምሯል። ኤአይን በተለያዩ ዘርፎች ላይ ለመጠቀም የሚያስችሉ ምርምሮችን አከናውኗል።
በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ኤአይ ላይ የተመረኮዙ ፕሮጀክቶችን መርቷል። ላለፉት 7 ዓመታት ወደ አፍሪካ ተመልሶ በመጀመሪያ በአይቢኤም የኤአይ ታማኝነት ላይ ሠርቷል።
በመቀጠልም በማይክሮሶፍት የአፍሪካን ኤአይ ፎር ጉድ ላብ በማደራጀት አየመራ ይገኛል። እስካሁን ድረስ ሥራዎቹን ከ100 በላይ በሆኑ ዓለም አቀፍ ሳይንሳዊ መድረኮች ላይ ያሳተመ ሲሆን፤ ከ20 በላይ የፈጠራ መብቶች አስመዝግቧል።
አሁን ላይ ዋነኛ ሥራው ኤአይ በተለያዩ ዘርፎች መፍትሔ ሰጪ የሚሆንበትን መንገድ መፈለግ ነው።
ቴክኖሎጂን ማየት፣ ለመረዳት መሞከር፣ ከዚያም ለችግር መፍትሔ ማዋል የሚለው ላይ ማተኮሩን ቀጥሏል።
በአፍሪካ ያሉ የኤአይ መሠረታዊ የማኅበረሰብ ተነሳሽነቶችን በመደገፍ የአህጉሪቱ አቅም ግንባታ እንዲጠናከር ያግዛል።
ከመንግሥታት፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች፣ ከትርፍ አልባ ተቋማት እና ከትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር እና ምክር በመስጠት የኅብረተሰቡ ዋና ዋና ችግሮች በኤአይ እንዲፈቱ ይሠራል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"ከወረቀት ወደ ተግባር"
ዶ/ር ግርማው በተለይም በግብርና፣ በጤና እና በትምህርት ዘርፍ ያሉ ችግሮችን እንዴት በኤአይ መፍታት ይቻላል? የሚለውን ያጠናል።
ሳይንሱን "በወረቀት ላይ" ከማጥናት ወደ ተግባር የተሻገረው ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ሳለ እንደነበር ይናገራል።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት ለጤናው ዘርፍ ምን ይፈይዳል? የሚለውን በምሳሌዎች እንመልከት።
በቬትናም የሠራቸው ፕሮጀክቶች የሕክምና ባለሙያዎች መተግበር የሚችሉት ቴክኖሎጂ መፍጠር ላይ ያተኩራል።
አንደኛው የቴክኖሎጂ ውጤት የቴታነስ ታማሚዎች በሰውነታቸው ላይ ያሉ ምልክቶችን (physiological signals) መረጃ ሰብስቦ፣ አብላልቶ ያሉበትን ደረጃ የሚገልጽ ነው።
ሌላኛው ቴክኖሎጂ የእጅ፣ የእግር እና የአፍ በሽታ (HFMD) ከያዛቸው ልጆች መካከል ለየትኞቹ ሕክምና ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባ የሚለይ ነው።
ወረርሽኙ ሲነሳ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ሆስፒታል ይሄዳሉ። ሐኪሞች ለየትኞቹ ልጆች ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው ለመለየት ስለሚቸገሩ በኤአይ ታግዘው እንዲሠሩ ቴክኖሎጂው እንደተሠራ ዶ/ር ግርማው ያስረዳል።
እነዚህ ቴክኖሎጂዎች በአፍሪካም ሊተገበሩ የሚችሉ ናቸው። በአህጉሪቱ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ችግሮች መካከል የእናቶች እና ሕጻናት ጤና አንደኛው ነው።
የእናቶች እና ሕጻናት ሞት በየትኛው የአፍሪካ አገር ቀነሰ? ለምን ቀነሰ? የትኛው አካባቢስ አሳሳቢ ነው? የሚለውን ለመረዳት የተሠራውን የኤአይ ቴክኖሎጂ እንደ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል።
"ቴክኖሎጂውን በአፍሪካ ቀዳሚ ለምንላቸው ችግሮች ማዋል በጣም አስፈላጊ ነው" ሲል ባለሙያው ያስረዳል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አፍሪካ እና ኤአይ
ከላይ የተጠቀሱት ምሳሌዎች ሰው ሠራሽ አስተውሎት እንዴት ችግሮን ለመፍታት መዋል እንደሚችል ያሳያሉ።
በቴክኖሎጂው ውስጥ የአፍሪካ ውክልና ምን ያህል ነው? የሚለውን ደግሞ እናንሳ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለመጀመሪያ ጊዜ የኤአይ ባለሙያዎች ፓናል ማቋቋሙ ምን ያህል ጉዳዩ እንዳሳሰበው ይጠቁማል።
ቴክኖሎጂውን አንዳንዶች "ሩቅ" አድርገው ቢያስቡትም ስልካችን፣ ኮምፒውተራችን ወይም በበይነ መረብ የምናገኘው መረጃ በሰው ሠራሽ አስተውሎት እንደሚዘወር መዘንጋት እንደሌለብን ባለሙያው ይናገራል።
ኮምፒውተር መረጃ የሚያብላላበት እና ስሌት የሚሠራበት አቅም (computing) በከፍተኛ መጠን ማደጉ ቴክኖሎጂው በፍጥነት እንዲለዋወጥ ምክንያት ሆኗል።
እናም ቴክኖሎጂው ምንድን ነው? ያመጣው ዕድል ምንድን ነው? መጠንቀቅ ያለብንስ ከምንድን ነው? የሚለውን ማወቅ ያስፈልጋል።
ኤአይን "ሁሉን ቻይ፣ በጣም ፍፁም" ቴክኖሎጂ አድርጎ በማሰብ እና "ሊያጠፋን የመጣ ጠላት" አድርጎ በመውሰድ መካከል ያለው መንገድ ላይ "እውነታው" እንደሚገኝ ዶ/ር ግርማው ይናገራል።
የተመድ የኤአይ ፓናል በጤና፣ በትምህርት፣ በዲሞክራሲ፣ በግብርና፣ በሥራ እና በምጣኔ ሃብት ዘርፍ ቴክኖሎጂው ያለውን ሚና እንዲሁም ለወደፊት የሚመጣውን አስቀድሞ ለማሳየት ይሠራል።
አሁን ባለው አካሄድ ብዙ ቴክኖሎጂዎች ሌላ ቦታ ተሠርተው በተዋረድ ወደ አፍሪካ ይመጣሉ። በዓለም አቀፉ ስብስብ የአፍሪካውያን ውክልና መኖር የአህጉሪቱን እውነታ የሚያሳይ እንደሆነ ባለሙያው ያስረዳል።
"የእኛ እውነታ ከሌላው ይለያል። እኔ እና ሌሎች አፍሪካውያን ባለሙያዎች በዚህ ፓናል ውስጥ መኖራችን የኤአይን አቅጣጫ ለመቀየስ በሚደረጉ ንግግሮች ላይ የእኛን እውነታ፤ በሐሳብ ላይ በተመረኮዘ ሳይሆን ካለን ልምድ እና የዕለት ከዕለት ሥራ ተነስተን ለሌሎችንም እውነታውን እንድናጋራ ያደርጋል።"
ኤአይ ምን መምሰል አለበት? በሚለው ውይይት ውስጥ ባለሙያዎቹ የአፍሪካን እውነታ እና አማራጮች በማካተት የእኩልነት ሚና ለመጫወት ጥረት ያደርጋሉ።
በቴክኖሎጂው ዘርፍ የአፍሪካ ተሞክሮ የተነፈገውን ጊዜ እና ቦታ ለማሻሻልም ይፈልጋሉ።
የአፍሪካን እውነታ እና ተሞክሮ መሠረት ያደረገ ሰው ሠራሽ አስተውሎት በተሻለ መጠን ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚውል ይናገራል።
ኤአይ 'ቅዱስ ወይስ እኩይ?'
ዶ/ር ግርማው እንደሚለው ሰው ሠራሽ አስተውሎትን "ጥግ ከማስያዝ" ይልቅ ቴክኖሎጂውን መረዳት ያስፈልጋል።
ሁላችንም በኪሳችን ስማርት ስልክ እስከያዝን ድረስ ኤአይን "በጣም ሩቅ" ሐሳብ አድርጎ መመልከት እንደማይቻል ይናገራል።
ቴክኖሎጂውን ፍፁም ችግር ፈቺ ወይም ዋነኛ የችግር ምንጭ አድርጎ መመልከትን ይነቅፋል።
"ሁሉን ቻይ አይደለም" የሚለው ሰው ሠራሽ አስተውሎት፤ በየትኞቹ ችግሮች ላይ መተግበር እንዳለበት መለየትን ይመክራል።
በጣም ሩቅ በሆነ እና የግብዓት ውስንነት ባለበት አካባቢ በኤአይ ታግዞ ሕክምና መስጠት ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሰሃራ በታች ያለው አፍሪካ 24% የዓለም የበሽታ ሸክም ያለበት ሲሆን ያለው የጤና ባለሙያ ሃይል 3% ብቻ ነው።
ነገር ግን ኤአይ ሁሉንም ሥራ ሊተካ የሚችል ተደርጎ መወሰድ የለበትም።
"ኤአይ መሬት ወርዶ አርሶ እኛን አይመግብም" የሚለው ባለሙያው፤ የሰው ልጆች የሚተኩት በኤአይ ሳይሆን "ኤአይን በሚያውቅ ባለሙያ" የሚለውን አተያይ ይደግፋል።
እናም ሰው ሠራሽ አስተውሎት "ያደጉ አገሮች" ወይም "የትልልቅ ተቋማት" ጉዳይ ነው ብሎ ራስን ማግለል አደጋ እንዳለው ይናገራል።
ቴክኖሎጂውን ማኅበረሰብ ተኮር ማድረግ ከሚቻልባቸው መንገዶች አንዱ በአፍሪካ ቋንቋዎች ያለውን ክህሎት ማሳደግ ነው።
በዋና ዋና የቋንቋ ሞዴሎች የሥልጠና ዳታ ውስጥ ከአፍሪካ የሚመጡ መረጃዎች ከ1% በታች መሆናቸውን ይጠቅሳል።
ከአፍሪካ በቂ መረጃ ከሌለ "ከኤአይ የሚወጣው ነገር አጠያያቂ ይሆናል" ይላል ዶ/ር ግርማው።
ኮምፒውተር መረጃ የሚያብላላበት እና ስሌት የሚሠራበትን አቅም (computing) ስንመለከት ከዓለማችን ከ75 እስከ 80 የሚሆነው አቅም በአሜሪካ እና ቻይና ይገኛል።
ባለሙያው እንደሚለው፤ አፍሪካ ከዓለም የዳታ ማዕከል እና የኮምፒውት አቅም ከ1% በታች ብቻ ስለምትይዝ "የዲጂታል ሉዓላዊነት ተግዳሮት" ተጋጥሟታል።
ይህም በአብዛኛው ደቡብ አፍሪካ እንደሚገኝ የሚጠቅሰው ባለሙያው፤ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ቁልፍ እንደሆነ ይናገራል።
ጥናቶች አንደሚያሳዩት 5% ብቻ የሚሆኑ የአፍሪካ ኤአይ ተመራማሪዎች በቂ የኮምፒውት አቅም ሲያገኙ፣ 95% የሚሆኑት ግን በውስን ሃብት ይሠራሉ።
ወጣቶች ክህሎታቸውን አዳብረው ከሚመጣው ቴክኖሎጂ ጋር እንዲተሳሰሩ ማሠልጠንም የግድ ይሆናል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኤአይ- እውነት እና ውሸትን የመለየት ፈተና?
"እናንተ እንድታግዙኝ የምፈልገው እውነትን ለገሀዱ ዓለም በማውጣት ነው። እውነት የለም ወይ? የሚያስብሉ ድርጊቶች እና አስተያየቶች እያየን ነው።"
የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ዓለም አቀፉን የኤአይ ፓናል ሲያስጀምሩ ይህንን መናገራቸውን ዶ/ር ግርማው ይገልጻል።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት እውነትን ለመለየት በሚያስቸግር መጠን መሠራቱን ቀጥሏል። በዚህ ረገድ ባለሙያዎች በሥነ ምግባር እንዲታነጹ ማድረግ (AI Ethics) የራሱ ድርሻ ቢኖረውም በተጠቃሚዎች ዘንድም ጥንቃቄ እንደሚያሻ ባለሙያው ይመክራል።
አንደኛው ሰው ሠራሽ አስተውሎትን ለምን አገልግሎት መጠቀም አለብን? የሚለውን በአግባቡ መለየት ነው።
ለዚህም የምግብ እጥረት፣ የጤና ባለሙያዎች ውስንነት እና የአየር ንብረት ለውጥ የጋረጡትን አደጋ ማንሳት ይቻላል።
300 ሚሊዮን ሰዎች ያለ ምግብ በሚያድሩበት (ዓለም አቀፉ የምግብ ድርጅት- ፋኦ ባስቀመጠው አሐዝ) እና ለ10 ሺህ ሰዎች ሦስት የጤና ባለሙያዎች ባሉበት (የዓለም ጤና ድርጅት ባስቀመጠው አሐዝ) የአፍሪካ አህጉር ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ችግሮች መለየት እንዳለባቸው ይናገራል።
እንደ አይኢኤ ሪፖርት በሰሃራ በታች አፍሪካ ውስጥ 600 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች አሁንም የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት የላቸውም።
"ችግሩንም ቴክኖሎጂውንም ማወቅ አስፈላጊ ነው። ዝም ብሎ መጥቶ የሚጫን ሳይሆን ቴክኖሎጂው እንዴት ነው የሚሠራው? እንዴት ነው ማወቅ አለማወቁ የሚታየው? የሚለው መለየት አለበት" ይላል።
ለዚህ መሠረቱ ደግሞ ከኤአይ የሚወጣ ነገር ሁሉ እውነተኛ እና ትክክለኛ ነው ብሎ አለመውሰድ ነው።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚሰጠው መረጃ ምን ያህል ትክክል ነው? የእርግጠኛነት መጠኑ ምን ያህል ነው? መቼ እና እንዴት ነው የሚሳሳተው? የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳት ያስፈልጋል።
ከፈጣኑ የኤአይ ለውጥ እኩል መራመድ ይቻላል?
ሰው ሠራሽ አስተውሎት እየተራቀቀ ቢሄድም የዓለም መሠረታዊ ነገሮች ሁሌም ስለሚኖሩ ችግር ፈቺ ክህሎቶችን በማዳበር ለመጪው ዓለም መዘጋጀትን ዶ/ር ግርማው ይመክራል።
"በኤአይ ስለመጠቀም ስናስብ ልንፈታው የምንችለውን ችግር ልናውቀው ይገባል። ኤአይ ስለመጣ ፍርድ ቤት፣ ፋይናንስ ወይም ጤና ተቋም ገብቶ ሁሉን አይፈታም። ስለዚህ መሠረታዊ ነገሮችን ተረድቶ ይሄን ቴክኖሎጂ ተጠቅሜ የተሻለ ምን መሥራት እችላለሁ? የሚለው ይከተላል።"
ሰው ሠራሽ አስተውሎትን እንደ መሣሪያ በመጠቀም "መስፈንጠር" እንደሚቻል ያስረዳል።
ባለሙያው እንደሚለው፤ በፍጥነት በሚለዋወጠው ዓለም አንድ ነገር ብቻ ተምሮ በዚያ ሁሉንም ነገር ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ፤ ሁሌ አዳዲስ ነገሮችን አውቆ ወደ ተግባር መቀየር የተሻለው መንገድ ነው።
ይህንንም "አዲስ ነገሮችን ቶሎ የመማርን ልምድ ማካበት ያስፈልጋል" ሲል ይገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኤአይ አርሶ ባያበላም ግብርናን እንዴት ይለውጣል?
በዚህ ጽሑፍ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በተሻለ መጠን ተገንዝቦ ለአሁናዊ ችግሮች መተግበርን ተመልክተናል።
እንደ መደምደሚያ በግብርናው ዘርፍ ሊኖረው የሚችለውን ሚና እንመልከት።
ግብርና፤ ኤአይ በጎ ተጽዕኖ ያመጣበታል ተብለው ከሚታሰቡ ዘርፎች ግንባር ቀደሙ ነው።
በአፍሪካ ከ33 እስከ 150 ሚሊዮን የሚደርሱ ጥቃቅን እና አነስተኛ አርሶ አደሮች ቢኖሩም ከቴክኖሎጂ ርቀዋል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ባወጣው ሪፖርት- ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት በአውሮፓውያኑ 2030 ከግብርና የሚያገኙት የአገር ውስጥ ዓመታዊ ጥቅል ምርት ወደ 1.2 ትሪሊየን ዶላር ይደርሳል። ከዚህም ግብርና ወደ 200 ቢልየን ዶላር ይደርሳል።
በአህጉሪቱ ትልቁ ቀጣሪ እና ገቢ ማግኛ የሆነው ግብርና የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ የተለያዩ ችግሮች ተደቅነውበታል።
"መሬቱ በጣም ታርሷል ስለዚህ ምርታማነቱ ቀንሷል። የአየር ንብረት ለውጥም አለ" የሚለው ዶ/ር ግርማው፤ ኤአይ ግብርናን ሊለውጥ የሚችላባቸውን መንገዶች ያስረዳል።
የመጀመሪያው የእርሻ መሬቶች የት ነው ያሉት? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ነው።
"የእርሻ መሬት የት ነው? ስፋቱ ምን ያህል ነው? የሚለው በጣም ቀላል የሚመስል መረጃ በአብዛኛው የአፍሪካ አገር አሁንም ክፍተት አለበት።"
በኬንያ፣ የተለያዩ ግዛቶች የእርሻ መሬትን ለመለየት የተዘረጋውን ቴክኖሎጂ እንደ ምሳሌ ይጠቀሳል። ይህ መረጃ የእርሻ መሬትን ለይቶ ሆስፒታል፣ መንገድ ወይም ሌላ መሠረተ ልማት የት ጋር መገንባት እንዳለበት ለመወሰን ይውላል።
ሌላኛው ዶ/ር ግርማው የሚጠቅሰው ማሳያ የመስኖ ውሃ መጠንን ለማወቅ የሚውለው ቴክኖሎጂ ነው።
ከሚገባው በላይ የመስኖ ውሃ ላለመጠቀም እና በጊዜ ሒደት ውሃው እንዳይደርቅ ለመከላከልም ይረዳል።
ባለፉት አሥርታት ጥቅም ላይ የዋለውን የመስኖ ውሃ በማወቅ የወደፊቱን ለመተንበይም ያግዛል።
ባለሙያው የሚጠቅሰው 'አዳፕት አፍሪካ' የተባለ ፕሮጀክት- የእርሻ መሬትን ማወቅ፣ የሚዘራውን ሰብል መለየት፣ ምን ያህል ምርት እንደሚገኝ መገመት፣ የአየር ንብረት ለውጥን ፈተና አስቀድሞ መገንዘብ፣ ለአርሶ አደሮች ድጋፍ መስጠት፣ የምርት መጠንን እንዲሁም የገበያ ሁኔታን መተንበይን ያካትታል።
ባለሙያው እንደሚለው፤ በአሁኑ ወቅት በኬንያ ያለው ድርቅ በበቆሎ ምርት ላይ እያሳደረ ያለውን ተፅዕኖ እየገመገሙ ነው።
ይህም "የአገሪቱን የምግብ ዋስትና ሁኔታ ቀድሞ ለመረዳትና ተገቢ የሆኑ የጣልቃ ገብነት እርምጃዎችን በወቅቱ ለመውሰድ እጅግ ወሳኝ ነው" ይላል።
'አዳፕት አፍሪካ' ፕሮጀክት የበርካታ የመንግሥት ተቋማት፣ የአካባቢ፣ የክልል እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች የጋራ ትብብር ውጤት ሲሆን፤ የተባበሩት መንግሥታት ተቋማትን፣ ትርፍ አልባ ድርጅቶችን፣ ጀማሪ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን እና ዩኒቨርሲቲዎችን በአንድ ላይ ያሰባስባል።
ይህም ሰው ሠራሽ አስተውሎት በኢትዮጵያ እና በተቀረው አፍሪካ እንዴት ሊተገበር እንደሚችል ሁነኛ ማሳያ ይሆናል።















