ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ነፍሰ ጡር የነበረች የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ፍቅረኛውን የገደለው የኬንያ የቀድሞ ባለሥልጣን ጥፋተኛ ተባለ
የቀድሞው የኬንያ ካውንቲ አስተዳዳሪ ኦኮት ኦባዶ ነፍሰ ጡር የነበረችው የ26 ዓመቷ የዩኒቨርስቲ ተማሪ ፍቅረኛውን በመግደሉ ጥፋተኛ ተባለ።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2018 ሻሮን ኦቲየኖ በደም የተለወሰ አስከሬን ከምዕራብ ኬንያ ራቅ ብሎ በሚገኝ ጥቅጥቅ ያለ ስፍራ ላይ ተጥሎ ተገኝቷል።
ወንጀሉ በተፈጸመበት ወቅት የሚጎሪ ካውንቲ አስተዳዳሪ የነበረው ኦባዶ እንዲሁም ሁለት ተባባሪዎቹ ሐሙስ ዕለት ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው የፍርድ ውሳኔ ተሰጥቷቸዋል።
የኦቲየኖ ሞት ከፍተኛ ተቃውሞ የቀሰቀሰ ሲሆን በአገሪቱ በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ምን ያህል የከፋ መሆኑን ያሳያል ተብሏል።
እአአ በ2022 በመላ አገሪቱ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ቢያንስ 34 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች አካላዊ ጥቃት ያጋጥማቸዋል።
ጉዳዩን ሲከታተሉ የነበሩት ዳኛ ሲሲሊያ ጊቱአ ውሳኔውን ሲያነብቡ ኦባዶ "ኦቲየኖን ለማስወገድ አሲሯል" ብለዋል።
አክለውም "እንድትገደል ለወንጀለኛ ቡድኖች ምክንያት አቅርቧል፣ አነሳስቷል እንዲሁም ገንዘብ ከፍሏል" ሲሉ ዘርዝረዋል።
የኦባዱ የቀድሞ የግል ረዳቱ የነበረው ማይክል ኦያሞ "ግድያውን በማመቻቸት" እና የቀድሞው የካውንቲው የመዝገብ ቤት ሠራተኛ ካስፓል ኦቢየሮ "የቦታ እና መኪና ድጋፍ በማድረግ እና የወንጀሉን ደብዛ ለማጥፋት በመጣር" ወንጀለኛ ሆነው መገኘታቸውን ዳኛዋ ተናግረዋል።
ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ናቸው ያላቸው ሦስቱም ግለሰቦች በማረሚያ ቤት ይገኛሉ።
"በፍርድ ውሳኔው ደስተኛ ነን፤ በስተመጨረሻም ፍርድ ለሻሮን እንደተሰጣት እናምናለን" ያሉት የሟች ቤተሰብ ጠበቃ ናቸው።
የኦቲየኖ ሞት ከተሰማ በኋላ የኔሽን ሚዲያ ጋዜጠኛ የሆነው ባራክ ኦዶኡር ከመሞቷ በፊት ከባለሥልጣኑ ጋር ስላላት ግንኙነት ልታነጋግረው እንደምትፈልግ ገልጻ ደውላለት እንደነበር በመሰማቱ ኬንያውያን በእጅጉ ተቆጥተው ነበር።
ጋዜጠኛዋ እና ኦቲየኖ በተገናኙበት ወቅት በፍጥነት እየተሽከረከረ የነበረ መኪና መጥቶ እርሷን አግቶ ሲወስድ እርሱ ግን አምልጧል።
ከሁለት ቀናት በኋላ የኦቲየኖ አስከሬን ሲገኝ መደፈሯን የሚያሳይ ማስረጃ የተገኘ ሲሆን አንገቷን፣ ሆዷ ላይ እና ከጀርባዋ ላይ ደግሞ በስለት ተወግታ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።
ጋዜጠኛው ስትታገት መመልከቱ ለምርመራው እንደ ቁልፍ ማስረጃ በመሆን አገልግሏል።
ፖሊስ አጋቾቹ የተጠቀሙትን መኪና ማግኘት ችሏል።
እገታው ተፈጸሟል በተባለበት ወቅት የመኪናው መከታተያ እንዳይሰራ ተደርጎ የነበረ ሲሆን በሚቀጥለው ቀን ደግሞ እንዲሰራ ተደርጓል።
እአአ በ2018 ጉዳዩን የያዙት ዋና አቃቤ ሕግ ኖዲን ሃጂ "ገዳዮቹ የተጠርጣረውን መኪና እንቅስቃሴ ለመደበቅ ሆን ተብሎ በተሰላ እርምጃ" መከታተያውን ማጥፋታቸውን መግለጫ በሰጡበት ወቅት ተናግረው ነበር።
በምርመራ ወቅት ኦባዶ እና ኦቲየኖ "ጥብቅ ግንኙነት" እንደነበራቸው የታወቀ ሲሆን "ሟች በማረገዟ አስተዳዳሪው ደስተኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል" ብለው ነበር።
እአአ በ2018 ኦባዶ በግድያው ላይ እጁ አንደሌለበት ገልጾ ተከራክሯል። ጠበቃዎቹ ሁለቱ የነበራቸው የፍቅር ግንኙነት በይፋ የሚታወቅ ሲሆን ምንም የሚያሳፍር ወይንም ነውር የለበትም ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ነገር ግን ፍርድ ቤቱ ይህንን ውድቅ አድርጎታል።
ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ በነበረበት ወቅት አቃቤ ሕግ 42 ምስክሮችን ያቀረበ ሲሆን የቀድሞው አስተዳዳሪ እና ሁለቱ ተባባሪዎቻቸው ኦቲየኖን ለመግደል በጋራ መስራታቸውን አስረድተዋል ሲል የኬንያ ስታር ጋዜጣ ዘግቧል።