ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የየመን ሁቲዎች ለኢትዮጵያ ቅርብ በሆነው የቀይ ባሕር ክፍል ላይ የጣሉት እገዳ የፈጠረው ስጋት
የኢራን አጋር የሆኑ ኃይሎች በቀይ ባሕር የመርከቦች መተላለፊያ መስመር ላይ የጣሉት እገዳ በዓለም የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ተጨማሪ መደናቀፍ ይሆናል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።
ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በመዝጋቷ በፋርስ ባሕረ ሰላጤ የመርከቦች እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጫና ተፈጥሯል። አጋሮቿ ደግሞ በቀይ ባሕር በኩል ሌላ ግንባር ለመክፈት ሲዝቱ ቆይተዋል።
አሁን ሰሜናዊ የመንን የሚቆጣጠሩት እና በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች የዓለም 12 በመቶው የነዳጅ ፍጆታ የሚጓጓዝበት ወደ ቀይ ባሕር በሚያስገባውን የባብ ኤል መንደብ ወሳኝ የባሕር መተላለፊያ በኩል የአሜሪካ ወዳጅ የሆነችው የሳዑዲ አረቢያ መርከቦች እንዳያልፉ ዕገዳ ጥለዋል።
ሰኞ ሐምሌ13/2018 ዓ.ም. የሁቲ ወታደራዊ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሪ እንደተናገረው በመርከቦቿ ላይ ዕቀባው የተጣለው ሁቲዎች በሚቆጣጠሯቸው አካባቢዎች በሚገኙ ወደቦች እና የአውሮፕላን ማረፊያዎች ላይ ሳዑዲ ለጣለችው ዕገዳ አጸፋ ነው።
በምላሹም የሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ክሱን አውግዞ አገሪቱ "በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት የመርከቦቿን ለመከላከል አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃዎችን ትወስዳለች" በማለት ዝቷል።
ሁቲዎች ከአስር ዓመት በፊት በሰነዓ የነበረውን የአገሪቱን መንግሥት ካስወገዱ በኋላ የመን በእርስ በርስ ጦርነት ወድማለች። የየመንን መንግሥት ወደ ሥልጣን ለመመለስ በሳዑዲ የሚመራው የአረብ አገራት ጥምረት ጣልቃ በመግባቱ ግጭቱ ተባብሷል።
አስራ ሁለት ዓመታት ባስቆጠረው ጦርነት ከ150 ሺህ በላይ ሰዎች የሞቱ ሲሆን፣ በተባበሩት መንግሥታት ግምት መሠረት ከ22 ሚዮን በላይ ሰዎች ለእርዳታ ፈላጊነት ያጋለጠ በዓለም ከሚጠቀሱ የሰብአዊ ቀውሶች አንዱ እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል።
ሁቲዎች ከሳዑዲ ወደቦች የሚነሱ እና ወደ ሳዑዲ የሚያመሩ መርከቦች በደቡባዊ ቀይ ባሕር በኩል እንዳያልፉ በማገዳቸው በርካታ መርከቦች አቅጣጫቸውን ለመቀየር ተገድደዋል።
በእርግጥ ሁቲዎች ወሳኙን የባብ ኤል መንደብ ወሽመጥን በመዝጋት የሳዑዲ መርከቦች እንዳያልፉ ማድረግ ይችላሉ?
መቀመጫውን ለንደን ባደረጋው የቻተም ሐውስ የባለሙያዎች ስብስብ ውስጥ የመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች ባለሙያ የሆኑት ፋራይ ኤል-ሙስሊሚ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሁቲዎች የባሕር ላይ እንቅስቃሴውን ለማደናቀፍ የጦር መሳሪያ አቅሙ አላቸው።
"ሁቲዎች የባሕር ላይ ፈንጂዎች ያሏቸው ሲሆን፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የባሕር ላይ ድሮኖች የመጠቀም አቅማቸውን አሳድገዋል" ብለዋል።
ስለዚህም በቀይ ባሕር ላይ የእንቅስቃሴ እገዳ ሳይጥሉ በአካባቢው ችግር የመፍጠር አቅም አላቸው።
ሙስሊሚ እንደሚሉት ሁቲዎች ቀውሱን ለመፍጠር ማድረግ ያለባቸው "አንድ ዒላማ ብቻ መምታት ነው። ምንም እንኳን ማሳያ ቢሆንም በኢንሹራንስ፣ በመርከብ እና በነዳጅ አቅራቢ ኩባንያዎች ላይ ፍርሃትን ይፈጥራል። ይህም ሰዎች ከሚያስቡት በላይ ከፍተኛ ጉዳትን ያስከትላል።
"ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ የኢራን ስትራቴጂ ደግሞ በቀጣናው ያሉ የአሜሪካ አጋሮች እንዲጎዱ ማድረግ ነው። ሁሉም ወደ ጦርነቱ እንዲገቡ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ነው።"
ቀደም ሲል ኢራን "ሌላ ግንባር እንደምትከፍት" ስታስፈራራ የነበረ ሲሆን፣ የየመን ጉዳዮች ባለሙያ የሆኑት አንዋት አል-አንሲ እንደሚሉት ደግሞ ሁቲዎች የኢራንን ፍላጎት ለማሳካት ሳዑዲ አረቢያን ወደ ግጭቱ ለመሳብ እየጣሩ ነው።
"ኢራን ያላት ብቸኛው አማራጭ በመሆኑ ይህ ሁኔታ የበለጠ መካረሩን ትፈልገዋለች። ሳዑዲዎች ከኢራን ጋር መጋፈጥን ሲያርቁት የቆዩ ቢሆንም፣ ሁቲዎች የሚያጠቁ ከሆነ ጥቅማቸውን ለማስከበር እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል" ብለዋል አንሲ።
"የባብ ኤል-መንዳብ ወሽመጥ ከዓለም ስትራቴጂካዊ የባሕር ወሽመጦች አንዱ እንደሆነ ይቆጠራል። ኢራን በወሽመጡ ላይ ስጋት የመደቀን ፍላጎትም ሆነ ችሎታ አላት" ሲሉ ከእስላማዊው አብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት ያላቸው ወታደራዊ መኮንን መናገራቸውን ታስኒም የተባለው የኢራን ዜና ወኪል ከሳምንታት በፊት ዘግቦ ነበረ።
ባብ ኤል-መንደብ ለምን አስፈላጊ ሆነ?
የባብ ኤል-መንደብ ወሽመጥን በቀይ ባሕር እና በአረቢያ ባሕር በየመን፤ በአፍሪካ ቀንድ በጂቡቲ እና በኤርትራ መካከል ይገኛል። ከሕንድ ውቅያኖስ እና ከኤደን ባሕረ ሰላጤ የሚመጡ መርከቦች ወደ ሱዊዝ ቦይ ለመድረስ በወሽመጡ በኩል ማለፍ ይጠበቅባቸዋል።
በ115 ኪ.ሜ ርዝመት እና 36 ኪ.ሜ ስፋት አለው። በአውሮፓውያኑ 1869 የሱዊዝ ቦይ መከፈቱ ወሽመጡን በዓለም አቀፍ ንግድ ውስጥ የማይተካ አገናኝ መተላለፊያ አድርጎታል። ይህም በአውሮፓ እና በእስያ መካከል አጭሩ የባሕር መንገድ እንዲሆን በር ከፍቷል።
የቀይ ባሕር ኮሪደር በጣም ሥራ ከሚበዛባቸው የመርከብ መስመሮች አንዱ ሲሆን፣ ከዓለም የባሕር ትራፊክ ውስጥ አንድ አራተኛውን ያህል ያስተናግዳል።
የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመጥ ተዘግቷል በሚባልበት ደረጃ ላይ ይገኛል። የባብ ኤል-መንደብ ወሽመጥ ከተዘጋ ተጨማሪ 12 በመቶ የዓለምን ነዳጅ አቅርቦት ይናጋል።
እንደ አሜሪካ የኢነርጂ መረጃ አስተዳደር ገለጻ ከመካከለኛው ምሥራቅ እና ከእስያ አገራት ወደ ምዕራብ የሚጓጓዝ አምስት ሚሊዮን በርሜል የሚገመት ነዳጅ በየቀኑ በወሽመጡ በኩል ያልፋል።
በተጨማሪም 8 በመቶ የሚሆነው የዓለም ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ በዚሁ መስመር ስለሚተላለፍ ወሽመጡን ለዓለም አቀፍ የኃይል አቅርቦት ወሳኝ የደም ሥር ያደርገዋል።
የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋቱን ተከትሎ ቀይ ባሕር በዓለም አቀፍ ንግድ ውስጥ ጠቀሜታው ከፍ ብሏል። ሳዑዲ አረቢያ ከያንቡ ወደብ ነዳጅ ለማጓጓዝ ባብ ኤል-መንደብን መጠቀም ጀምራለች። ሪያድ በየቀኑ ከምሥራቃዊ ነዳጅ ማውጫዎቿ በቧንቧ በሚሊዮን የሚቆጠር በርሜሎችን ታስተላልፋለች።
ከድፍድፍ ነዳጅ እና ከጋዝ በተጨማሪ፣ የባብ ኤል-መንደብ ወሽመጥ በምሥራቅ እና በምዕራብ መካከል ያለ ዋና የንግድ መስመር ሲሆን፣ በየቀኑ በደርዘን የሚቆጠሩ የጭነት መርከቦች በዚሁ መስመር በኩል ያልፋሉ።
መስመሩ ከተዘጋ በ2021 የፓናማ የጭነት መርከብ ኤቨር ጊቨን የስዊዝ ቦይን በመዝጋት የፈጠረችውን ዓይነት ተጽዕኖ በዓለም የነዳጅ እና የምርቶች እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጫናን ይፈጠራል።
በወቅቱ በዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለቶች ላይ ከባድ ማነቆዎች ተፈጥሮ ነበር። ይህም የነዳጅ አቅርቦትን እና የተለያዩ እቃዎችን ጉዞ ከማዘግየቱም በተጨማሪ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አስከትሏል።
የሁቲዎች ሚና
በባብ ኤል-መንደብ ወሽመጥ ላይ የሚሰነዘረው ማንኛውም ጥቃት በኢራን በሚደገፈው እና መቀመጫውን በየመን ባደረገው በሁቲ በኩል ሊሆን ይችላል።
ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ አንድ የሁቲ መሪ ቡድኑ ቴህራንን በመደገፍ የባብ አል-መንደብ ወሽመጥን ለማጥቃት "በወታደራዊ መንገድ ዝግጁ" መሆኑን ለሮይተርስ ተናግሯል።
አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ ከአንድ ወር በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁቲዎች ከቀናት በፊት እስራኤል ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል። እስራኤል ከየመን የተሰነዘሩባትን ሁለት ሚሳዔሎችን እንደተኮሰች ተናግራለች።
ቡድኑ የየመንን የቀይ ባሕር ዳርቻዎች የሚቆጣጠር ሲሆን፣ በጋዛ ጦርነት ወቅት የባብ አል-መንደብ ወሽመጥን ዒላማ አድርጎ ነበር። ሁቲዎች ከ100 በላይ የንግድ መርከቦችን በሚሳዔል እና በድሮን አጥቅተው ሁለት መርከቦችን ያሰመጡ ሲሆን፣ አራት መርከበኞችን ገድለዋል።
ቡድኑ ኅዳር 2023 በቀይ ባሕር ላይ ሲንቀሳቀስ የነበር በጃፓን የተመዘገበ የዩናይትድ ኪንግደም የጭነት መርከብን ለመጥለፍ ሄሊኮፕተር ተጠቅሟል።
ሁቲዎች ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸውን መርከቦች ብቻ ዒላማ እንደሚያደርጉ ቢናገሩም፣ ጥቃቶቹ ያለልዩነት እንደሚደረጉ በሰፊው ተገልጿል። ይህም በርካታ የዓለማችን ትላልቅ የመርከብ እና የነዳጅ ኩባንያዎች አካባቢውን መጠቀም እንዲያቆሙ አስገድዷቸዋል።
ሁቲዎች እጅ እንደሰጡ አሜሪካ ስትገልጽ ሁቲዎች በበኩላቸው አሜሪካ ማፈግፈጓን በወቅቱ ገልጸው ነበር። ተንታኞች ጥቃቱን በድጋሚ ሊጀምሩ እንደሚችሉ ስጋት አላቸው።
"ጦርነቱ ከቀጠለ ሁቲዎች ይቀላቀላሉ ተብሎ ሁልጊዜም የሚጠበቅ ጉዳይ ነው" ስትል የቢቢሲዋ ዘጋቢ ሊስ ዱሴት ገልጻለች።
አክላም "ሰሜን ምዕራብ የመንን የሚቆጣጠሩት ሁቲዎች ቀይ ባሕርን ከዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮች ጋር የሚያገናኘውን የባብ አል-መንደብ ወሽመጥን የማስተጓጎል ትልቅ መሳሪያቸውን እስካሁን አልተጠቀሙም" ስትል አክላለች።
የአሜሪካ የትራንስፖርት መምሪያ የባሕር አስተዳደር በቅርቡ ባወጣው መግለጫ "ምንም እንኳን የሁቲ አሸባሪ ቡድን በጥቅምት ወር በእስራኤል እና በጋዛ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረገ ወዲህ የንግድ መርከቦችን ባያጠቃም፤ በአካባቢው የሚተላለፉ የንግድ መርከቦችን ጨምሮ የአሜሪካ ንብረቶች አሁንም አደጋ ላይ መሆናቸው ይቀጥላል" ብሏል።
ጫና ውስጥ የወደቀው ዓለም አቀፍ ንግድ
ባብ አል-መንደብ በአረብኛ "የእምባ በር" ወይም "የሐዘን በር" እንደማለት ነው። በአካባቢው የሚከሰቱትን ከጠንካራ ወጀብ እና ሊተነብይ ከማይችል ነፋስ እስከ የባሕር ላይ ወንበዴዎች እንዲሁም ግጭትን የመሳሰሉ አደጋዎችን ለተመለከተ ስሙ አካባቢውን ይገልጸዋል።
ከ2008 እስከ 2012 ባለው ጊዜ ውስጥ የባብ አል-መንደብ ወሽመጥ እና በዙሪያው ያለው ውሃ በርካታ የባሕር ወንበዴ ጥቃቶችን አስተናግዷል።
በዋናነት ጥቃቱ የሚፈጸመው በሶማሊያ ቡድኖች ሲሆን የመርከብ ሠራተኞችን አፍነው ገንዘብ ይጠይቃሉ። ክስተቶቹ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እና የመርከብ ኩባንያዎች በአካባቢው ያለውን ደኅንነት እንዲያጠናክሩ አስገድዷቸዋል።
የባሕር መስመሩ መዘጋት በሆርሙዝ ወሽመጥ ምክንያት የተዳከመውን የዓለም የነዳጅ እና የጋዝ አቅርቦትን የበለጠ በማወሳሰብ የዋጋ ንረቱን ያባብሰዋል።
በባሕረ ሰላጤው የተፈጠረው የመርከብ ጉዞ መስተጓጎል የብሬንት ድፍድ ነዳጅ ዋጋ ከጦርነቱ በፊት ከነበረበት 70 ዶላር ወደ ከ115 ዶላር በላይ እንዲደርስ አድርጎታል።
ከሸማቾች ምርቶች እስከ ግብርና ሸቀጦች ድረስ ያለው ዓለም አቀፍ ንግድም ተጽዕኖው እየደረሰው ነው። በሌላ የባሕር መስመር ላይ አዲስ መስተጓጎል መፈጠሩ ዋጋዎችን የበለጠ ከፍ ሊያደርግ እና በኢራን ጦርነት የተፈጠረውን የኢኮኖሚ ውድቀት ሊያባብሰው ይችላል።
መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው የባሕር ላይ እንቅስቃሴ ስጋቶች አማካሪ ተቋም ከሆነው 'ባሻ ሪፖርት' ሞሐመድ አልባሻ እንዳሉት ሁቲዎች ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሚያቀኑ መርከቦችን ዒላማ ማድረግ ሊጀምሩ የሚችሉበት ሁኔታ ስለመኖሬ ግልጽ አይደለም።
"ምንም እንኳን መርከቦች ላይ ጥቃት ባይፈጸምባቸውም የሰጡት ማስጠንቀቂያ ብቻውን የመርከቦች እንቅስቃሴን በማደናቀፍ በተወሰኑ የሳዑዲ ወደ ቦች ላይ ስጋትን ሊፈጥር ይችላል። ስለዚህም ሁቲዎች ከማስፈራራት ወደ ቀጥተኛ ጥቃት የሚሸጋገሩ ከሆነ አሳሳቢ ይሆናል" በማለት አልባሻ ለሮይተርስ ዜና ወኪል ተናግረዋል።