በፈረንሳይ እና በስፔን በሰደድ እሳት ምክንያት ከ300 ሺህ በላይ ሰዎች አካባቢያቸውን ለቅቀው ወጡ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በፈረንሳይ እና በስፔን ለቀናት በዘለቀውና በነፋስ እና በከፍተኛ ሙቀት ሳቢያ ለመቆጣጠር አዳጋች በሆነ ሰደድ እሳት ምክንያት ከ300 ሺህ በላይ ሰዎች አካባቢያቸውን ለቅቀው ወጡ።
የእሳት አደጋ ሠራተኞች በደቡብ ምዕራብ ፈረንሳይ የተከሰተውን ሰደድ እሳት ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ ቢሆንም ኃይለኛ ነፋስ እሳቱን ወደ ቦርዶውክስ ከተማ እየገፋው ነው።
በዚህም ተጨማሪ 55 ሺህ ሰዎች አካባቢያቸውን ለቅቀው እንዲወጡ ቅዳሜ ዕለት ተነግሯቸዋል።
ይህም ከደቡብ ምዕራብ ግዛቶች ጊሮንድ እና ላንድስ የተፈናቀሉ ሰዎችን ቁጥር ወደ 250 ሺህ አድርሶታል።
ኃይለኛ ነፋስ እና ደረቅ አየር ሰደድ እሳቱን ለመቆጣጠር አዳጋች እንዳደረገው የእሳት አደጋ ሠራተኞች እየገለጹ ነው።
ፈረንሳይ ለአደጋው ምላሽ ለመስጠት ጦሯን አንቀሳቅሳለች። ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ፈረንሳይ እንደገና እንደምትገነባ እና መንግሥታቸው አስፈላጊ እስከሆነ ድረስ ከጎናቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀባት ስፔንም እሳቱ በማድሪድ ከተማ አቅራቢያ እንደቀጠለ ነው።
የአገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ፣ "አስቸጋሪ ጊዜያት እንደሚኖሩ" የገለጹ ሲሆን የቫሌንሺያ ባለሥልጣናት አንድ ግለሰብ በእሳት አደጋው መሞቱን አረጋግጠዋል።
70 ዓመት እንደሚሆነው የተገመተው ግለሰብ መኪናው ውስጥ ሕይወቱ አልፎ በእሳት አደጋ ሠራተኞች ተገኝቷል።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፌርናንዶ ግራንዴ ማርላስካ፣ አሁን ያለው ሁኔታ ከትናንቱ የባሰ እንደሆነ አስረድተው " የአየር ሁኔታው እየረዳን አይደለም" ብለዋል።
ሁኔታውን "ውስብስብ" ሲሉ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ነፋሱ እሳቱን ወደ ደቡባዊ አቅጣጫ ይገፋዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
እንደ ሚኒስቴሩ መረጃ ከሆነ በስፔን አደጋው ከተከሰተ ጀምሮ ወደ 60 ሺህ ሰዎች ከማድሪድ እና አቪላ ግዛቶች የወጡ ሲሆን ወደ 28 ሺህ የሚሆኑት እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ እዚያው ይገኛሉ።
ቅዳሜ ምሽት በቶሌንዶ አቅራቢያ የሚገኙ ቢያንስ የስምንት ከተሞች ነዋሪዎች ከአካባቢው እንዲወጡ ታዝዘዋል። ምን ያህል እንደሆኑ ግን ቁጥራቸው አልተገለጸም።
የማድሪድ ግዛት ርዕሰ መስተዳድር ኢዛቤል ዲያዝ አዩሶ ሁኔታውን " በክልሉ ታሪክ ያጋጠመ አስከፊ አደጋ" ሲሉ ገልጸውታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሳንቼዝ፣ በስፔን በዚህ ዓመት 130 ሺህ ሔክታር መሬት መቃጠሉን ጠቅሰው ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ በአማካይ 100 ሺህ ሔክታር መሬት መውደሙን ገልጸዋል።
የፈረንሳይ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሎውረንት ኑኔዝ በበኩላቸው ከጥር ወር ወዲህ ወደ 98 ሺህ ሔክታር መሬት ወድሟል ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እያለ ሲሲሊ ደሴትን ጨምሮ በጣሊያን ከ350 በላይ ሰደድ እሳቶች ተከስተዋል። የደሴቷ ሲቪል ማኅበረሰብ ጥበቃ ባለሥልጣን ነዋሪዎች ከአካባቢው እንዲወጡ አዝዟል።
በስኮትላንድም አርብ ዕለት በኬርንጎርም ብሔራዊ ፓርክ ለ10 ተከታታይ ቀናት የዘለቀውን ሰደድ እሳት ለማጥፋት ርብርብር እየተደረገ ነው።
የአውሮፓ ኅብረት የአደጋ አስተዳደር ኮሚሽነር ሃድጃ ላህቢብ፣ በአውሮፓ የሰድድ እሳት ያስከተለው ጉዳት ከዚህ ቀደም ከተመዘገቡት ሪከርዶች ያየለ ነው ብለዋል።
ባለፈው ዓመት በበጋ ወቅት አንድ ሚሊዮን ሔክታር መሬት መቃጠሉን እና በዚህ ዓመት የበጋ ወቅት ቀደም ብሎ በመጀመሩ "ሌላ ታሪካዊ ክስተት" እንደሚጠበቅም ኮሚሽነሯ አክለዋል።
ኮሚሽነሯ ተጨማሪ አደጋዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉም አስጠንቅቀዋል።
የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዚደንት ኡርሱላ ኦን ዲር ሊን ፣ በስፔን እና ፈረንሳይ ያጋጠሙ አደጋዎችን ለመዋጋት 11 አውሮፕላኖች እና ሄሊኮፕተሮች መላኩን ገልጸዋል።















