ቀጥታ, ኢራን የብሪታኒያ ጦር ሠፈሮች “ሕጋዊ ዒላማ ናቸው” ማለቷን ተከትሎ ዩኬ “ራሷን ለመከላከል ዝግጁ” መሆኗን ገለጸች

ኢራን፣ የዩናይትድ ኪንግደም ጦር ሠፈሮች ለአሜሪካ ጥቃቶች ጥቅም ላይ እየዋሉ ስለሆነ “ሕጋዊ ዒላማ” እንደሆኑ መግለጿን ተከትሎ፤ የብሪታኒያ መንግሥት "ራሱን ለመከላከል 24/7 ዝግጁ" መሆኑን አስታወቀ። ከኢራን አብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት ያለው ታስኒም የዜና ወኩል ሐሙስ ዕለት ያወጣው መግለጫ፤ ከቀናት በፊት የተፈጸመው የአሜሪካ የድብደባ ተልዕኮ የተነሳው ከብሪታኒያው ጦር ሠፈር ‘ሮያል ኤር ፎርስ ፌር ፎርድ’ እንደሆነ ገልጿል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ተመድ 6 ሺህ መርከበኞች ከሆርሙዝ ወሽመጥ የሚወጡበት መንገድ እንዲፈጠር ጠየቀ

    ሆርሙዝ ወሽመጥ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ከሆርሙዝ ወሽመጥ አካባቢ መውጣት ያልቻሉ ወደ ስድስት ሺህ የሚጠጉ መርከበኞች መውጫ መንገድ ሊመቻችላቸው እንደሚገባ የመንግሥታቱ ድርጅት አሳሰበ።

    በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ተሳታፊ የሆኑ አካላት መርከበኞቹ ከሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲወጡ ተገቢውን ትብብር ማድረግ እንዳለባቸው አስታውቋል።

    የተመድ የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኪሚሽነር ቮልከር ቱርክ በሺህዎች የሚቆጠሩት መርከበኞች “ከፍተኛ ሰብአዊ እና የሰብአዊ መብት ቀውስ” እንደገጠማቸው ገልጸዋል። አፋጣኝ እርምጃ መወሰድ እንዳለበትም አሳስበዋል።

    ኢራን እና አሜሪካ ዳግመኛ ወደ ግጭት ከመመለሳቸው በፊት የተመድ የማሪታይም ተቋም ስድስት ሺህ መርከበኞች፣ በመቶዎች በሚቆጠሩ መርከቦች ውስጥ ሳሉ ከሆርሙዝ ወሽመጥ መውጣት እንዳልቻሉ ይፋ አድርጓል።

    እነዚህን መርከበኞች እስካሁን ድረስ ከቀጣናው ማስወጣትም አልተቻለም።

  2. አሜሪካ በርካታ አገራት ላይ አዲስ ታሪፍ ጣለች

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ባለፈው ዓመት ወደ ሥልጣን ከወጡ ወዲህ በድጋሚ የንግድ ጦርነትን ያቀጣጠሉት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ በ60 የአገሪቱ የንግድ አጋራት ላይ ታሪፍ ጣሉ።

    አዲሱ ዙር እርምጃ የተካተቱትን ዩናይትድ ኪንግደም፣ ቻይና እና አውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ በርካታ አገራት፣ ወደ አሜሪካ በሚልኳቸው ምርቶች ላይ ከ10 እስከ 12.5 በመቶ የሚደርስ ቀረጥ ይጠብቃቸዋል። ወደ አሜሪካ የሚገቡ ምርቶችን በሙሉ በሚባል ደረጃ ታሪፍ ተጥሎባቸዋል።

    ይህ ታሪፍ ከዚህ ቀደም ትራምፕ የጣሉትን እና ተፈጻሚነቱ ዛሬ አርብ የሚያበቃውን ተመሳሳይ ቀረጥ ውሳኔ የሚተካ ነው። ትራምፕ ይህንን እርምጃ የወሰዱት እነዚህ ቁልፍ የኢኮኖሚ አጋሮች የጉልበት ብዝበዛን ለማስቀረት አልቻሉም በሚል ነው።

    አሜሪካዊቷ የኢኮኖሚ ባለሙያ ካሮሊን ፍሬውንድ ግን ለእርምጃው የቀረበው ክስ ትራምፕ "ታሪፎቹን ለመጣል የሚያስችል ሕጋዊ ምክንያት ለመፈለግ" ሲሉ ያቀረቡት እንጂ “ለግዳጅ ሠራተኝነት ሲባል የተወሰደ አይደለም” ብለዋል።

    የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተያዘው የአውሮፓውያኑ 2026 መጀመሪያ ባስተላለፈው ውሳኔ፤ ከዚህ ቀደም የአደጋ ጊዜ አዋጅን በመጠቀም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተጣለው ታሪፍ ሕገ ወጥ እንደሆነ ገልጾ ነበር።

    ዋይት ሀውስ ባለፈው ወር ላይ የጉልበት ብዝበዛን ለማስቆም በቂ ሥራ አልተከናወነም የሚል ስጋት በማንሳት ከ10 እስከ 12.5 በመቶ ቀረጥ እንዲጣል ሀሳብ አቅርቦ ነበር።

    የአሜሪካ የንግድ መስሪያ ቤት ተወካይ ጄሚሰን ግሪር፤ “የዛሬው እርምጃ የሰብአዊ መብት ጥሰት እና አሳሳች የንግድ ልምምድ ላይ የሚታየውን [ችግር] ማስተካከል” እንደሚጀምር ተናግረዋል። በዚህ ምክንያት “በሁሉም ቦታ የሚገኙ ሠራተኞችን ደህንነት ያሻሽላል” ብለዋል።

    አዲሱ ቀረጥ በ60 የአሜሪካ የንግድ አጋራት ላይ የሚጣል ሲሆን የእነዚህ አጋራት ወደ አሜሪካ ከሚገባው ምርት ውስጥ 99.4 በመቶ እንደሚሸፍን ገልጸዋል።

    በ’ዩሲ ሳን ዲዬጎ’ የዓለም አቀፍ ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ትምህርት ቤት ዲን ፍሬውንድ ቀረጡን ለመጣል ስለቀረበው ምክንያት ከቢቢሲ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል። የኢኮኖሚ ባለሙያዋ፤ “እንደማስበው፣ ታሪፍ ለመጣል ሕጋዊ እና እርምጃውን ለማስጠበቅ የሚያስችላቸው ምክንያት እየፈለጉ ነበር” ብለዋል።

    “ምክንያቱም [የአሜሪካ የንግድ መስሪያ ቤት ተወካይ] ግሪር እና ትራምፕ በደንብ ግልጽ እንዳደረጉት ዋና ግባቸው ከንግድ ሚዛን ጉድለት ጋር የተያያዘ ነው። ለአሜሪካ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ሲባል ነው፤ ለጉልበት ብዝበዛ አይደለም” ሲሉም መልዕከታቸውን አብራርተዋል።

  3. በሰሜናዊ ኢራቅ በሚገኘው የአሜሪካ ጦር ሠፈር በርካታ ፍንዳታዎች ተሰሙ

    በኢርቢል አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ ፍንዳታዎች ከተሰሙ በኋላ ጭስ ታይቷል

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የምስሉ መግለጫ, በኢርቢል አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ ፍንዳታዎች ከተሰሙ በኋላ ጭስ ታይቷል

    የአሜሪካ ጦር በኢራን ለ13ኛ ሌሊት የፈጸመውን ድብደባ ማጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ በሰሜናዊ ኢራቅ በሚገኝ የአሜሪካ ጦር ሠፈር ተከታታይ ፍንዳታዎች መሰማታቸውን ኤፒ ዘገበ።

    የአሶሺዬትድ ፕሬስ ጋዜጠኛ አርብ ማለዳ የኢራቅ ከፊል ራስ ገዝ ግዛት በሆነው የኩርዶች ዋና ከተማ ኢርቢል አቅራቢያ ሰባት ፍንዳታዎችን መስማቱን ዘግቧል።

    በተጨማሪም ከጦር ሰፈሩ አቅራቢያ በሚገኝ የአውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ ወይም ውስጥ አራት ጭሶችን መመልከቱን ዘግቧል።

    የአሜሪካ እና ኢራን ጦርነት ዳግመኛ ካገረሸ በኋላ ቴህራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ እና በባሕረ ሰላጤው አገራት ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ቀጥላለች።

    የኢራን አጋር የሆኑት ሁቲዎችም በዚህ ሳምንት በቀይ ባህር ላይ የሚቀዝፉ ሁለት የሳዑዲ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን በመግለጽ ቀጣናው እንደ አማራጭ የሚተላለፍበት የባህር መስመር ላይ አደጋ ደቅነዋል።

    የኢራን ጤና ሚኒስቴር ዳግመኛ ጦርነቱ ካገረሸ በኋላ 55 ሰዎች መገደላቸውን እና ከ600 በላይ መጎዳታቸውን ይፋ አድርጓል።

    በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ የሚገኘው ይህ ጦርነት በኢራን እንዲሁም በመላው ዓለም ምጣኔ ሃብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።

    አሜሪካ ኢራንን ስትደበድብ ቴህራን በቀጣናው የሚገኙ በርካታ የአሜሪካ ጦር ሠፈሮችን ዒላማ አድርጋለች።

  4. ኢራን ለሁቲዎች ወታደራዊ አዛዦችን እና የሚሳዔል ቁሳቁሶችን መላኳን ሮይተርስ ዘገበ

    የሁቲ ታጣቂ ላውንቸር ይዞ

    የፎቶው ባለመብት, reuters

    ኢራን በዚህ ወር የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ አዛዦችን፣ ወታደራዊ አማካሪዎችን እንዲሁም ከሚሳዔል እና ድሮን ጋር የተያያዙ ቁሳቁሶችን ወደ የመን መላኳን ምንጮችን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘገበ።

    ቴህራን ይህንን እርምጃ የወሰደችው በየመን የሚገኙት አጋሮቿ ሁቲዎች፣ በቀይ ባሕር የሚደረጉ የመርከብ ጉዞዎች ላይ አደጋ እንዲጥሉ በማለም እንደሆነ ምንጮቹ ጠቅሰዋል።

    በጉዳዩ ላይ መረጃው ያላቸው አራት ምንጮች እንዲሁም የየመን ማስታወቂያ ሚኒስትር እና የቀጣው ደኅንነት ተንታኝ፣ ኢራን ወደ የመን ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ያጓጓዘችው እአአ ሐምሌ 13 ነው ሲሉ ለሮይተርስ ተናግረዋል።

    ለደኅንነታቸው በሚል ስማቸው እንዳይጠቀስ ጠየቁ ሁለት የኢራን ምንጮች የአብዮታዊ ዘብ አዛዦች ቁጥር ከ10 እስከ 21 የሚደርስ መሆኑን ለሮይተርስ ተናግረዋል። ከእነዚህም መካከል ከፍተኛ አዛዦች እንደሚገኙበት ገልጸዋል።

    ከኢራን የተነሳው አውሮፕላን በሁቲ ቁጥጥር ስር ወደሚገኘው ሰነዓ በረራ ቢያደርግም አውሮፕላን ማረፊያው በሳዑዲ ጥቃት ከደረሰበት በኋላ ግን ወደ ቀይ ባሕር ወደብ ከተማዋ ሆዴይዳህ ማምራቱን ዘገባው ያመለክታል።

    አንድ ምንጭ “የአብዮታዊ ዘብ አዛዦች ወደዚያ የተጓዙት የሁቲን ዘመቻዎች ለመደገፍ እንዲሁም በአዲስ የሚሳዔል ሥርዓት ላይ ስልጠና ለመስጠት ነው” ብለዋል።

    በተጨማሪም ኢራን የሁቲን እንቅስቃሴዎች ለመደገፍ በአውሮፕላኑ ወርቅ መላኳ ተጠቅሷል።

    ቴህራን በተደጋጋሚ በየመን የሚንቀሳቀሱት ሁቲዎችን የሚሳዔል አቅም ለመገንባት ምንም ዓይነት ድጋፍ እንዳላደረገች በመግለጽ ስታስተባብል ቆይታለች።

    የኢራን መንግሥት በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጥ ሮይተርስ ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም፥።

    አውሮፕላኑ ውስጥ እንደነበሩ የተናገሩት የሁቲ የሚዲያ ኃላፊ አብደል ራህማን አል አህኖሚ፣ ኢራን ወደ የመን ወታደራዊ ባለሙያዎችን ልካለች የሚለውን ክስ "ውሸት እና ፈጠራ" ሲሉ የገለጹ ሲሆን፣ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት ሁሉም ተሳፋሪዎች ሲቪሎች እንደነበሩም ተናግረዋል።

    ሁቲዎች ከዚህ ቀደም የኢራን ተቀጽላ መሆናቸውን ያስተባበሉ ሲሆን፣ የራሳቸውን የጦር መሣሪያዎች እንደሚያመርቱም ገልጸዋል።

    በየመን የሚንቀሳቀሰው ሁቲ ሳዑዲ አረቢያ አድርሳዋለች ባለው የሐምሌ 13 የሰነዓ አውሮፕላን ማረፊያ ድብደባ ምላሽ ለመስጠት፣ ሳዑዲ ላይ የባህር ላይ እገዳ መጣሉን ሰኞ ዕለት አስታውቋል።

    በሳዑዲ መንግሥት የሚደገፈው የየመን መንግሥት የማስታወቂያ ሚኒስትር ሞአመር አል ኢርያኒ በበኩላቸው፣ የኢራን አብዮታዊ ዘብ አዛዦች እና መሳሪያዎች ወደ የመን መምጣታቸውን ለሮይተርስ በስልክ በሰጡት ቃለ ምልልሰ ላይ አረጋግጠዋል።

    "ተልዕኳቸው የሚሊሻዎቹን ወታደራዊ አቅም ማጠናከር እና በቀይ ባሕር እና በባብ አል ማንዳብ የባህር መስመር ላይ ያለው ዓለም አቀፍ መተላለፊያ ደኅንነትን አደጋ ላይ እንዲጥሉ ማዘጋጀት ነው" ብለዋል።

  5. ትራምፕ የታገደው የኢራን ሀብት ጥቃት የተፈጸመባቸው መርከቦችን ለመጠገን እንደሚውሉ ተናገሩ

    መርከቦች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ የተያዙት የኢራን ሀብቶች “በመርከቦች፣ ጭነቶች ወይም የትኛውም ተያያዥ ነገር ላይ ለደረሰው ጉዳት” ክፍያ ለመፈጸም እንደሚጠቀሙበት ተናገሩ።

    የአሜሪካ ጦር በበኩሉ ለ13ተኛ ተከታታይ ምሽት ኢራን ላይ ጥቃት መፈጸሙን ያስታወቀ ሲሆን የቴህራን መገናኛ ብዙኃን ደግሞ አራት ሰዎች መገደላቸውን እና አምስት ሰዎች መሞታቸውን ዘግበዋል።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አባስ አራግቺ የትራምፕን አስተያየት “አቀጣጣይ ሁኔታ” ሲሉ ጠርተውታል።

    አሜሪካ ትናንት ምሽት ጥቃት የፈጸመችው፤ በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች በቀይ ባሕር ሲጓዙ የነበሩ ሁለት የሳዑዲ አረቢያ ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን መምታታቸውን ካስታወቁ በኋላ ነው። ይህ የሁቲ ጥቃት የዓለም የመርከብ ጉዞ ላይ ስጋት በመፍጠሩ የነዳጅ ዋጋ ጨምሯል።

    የአሜሪካ ጥቃትን ተከትሎ በኢራን ባንዳር አባስ የተባለው የወደብ ከተማ እና ቀሽም ደሴትን ጨምሮ በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል በሚገኙ ቁልፍ ወታደራዊ እና የንግድ ቦታዎች ላይ ፍንዳታዎች መከሰቱን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    ይህ ጥቃት ከመድረሱ አስቀድሞ ፕሬዝዳንት ትራምፕ፣ ሁቲዎች ወይም ኢራን ጥቃት የሚፈጽሙ ከሆነ ቴህራን ላይ “ትልቅ ወታደራዊ ቅጣት” እንደሚጥሉ ዝተው ነበር።

    የአሜሪካ ጦር የኢራንን በቀጣናው የሚጓዙ ሲቪሊያን መርከቦች ላይ ስጋት የመጣል አቅም ለማዳከም ያለመ ጥቃት መፈጸሙን ገልጿል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ባወጣው መግለጫ፣ “የኢራን ወታደራዊ የዕዝ ማዕከላትን፣ የድሮን ማከማቻዎችን፣ የኮሚዩኒኬሽን ኔትዎርኮችን፣ የባህር ዳርቻ የክትትል ስፍራዎች እንዲሁም የባህር ኃይል አቅሞችን" ዒላማ ማድረጉን አስታውቋል።

    አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የነበራትን ቁጥጥር መልሳ ለማግኘት ግፊት እያደረገች ባለችበት በዚህ ወቅት፤ በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች በቀይ ባሕር በኩል የሚደረግ የመርከብ ጉዞ ላይ አዲስ ስጋት ደቅነዋል።

    ይህንንም ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ከግንቦት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በበርሜል ከ100 ዶላር ተሻግሯል።

    ይህ ቀጣናዊ ውጥረት በቀጠለበት ሁኔታ፤ ፕሬዝዳንት ትራምፕ መርከቦች እና ጭነቶች ላይ ለደረሰው ጉዳት የሚሰጥ ካሳ “አሜሪካ እጇ በሚገኘው እና በምትቆጣጠረው የኢራን ገንዘብ እንደሚከፈል” ተናግረዋል። ለዚህ የሚውለው የገንዘብ መጠንም “እጅግ ከፍተኛ” ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።

    ለዚህ የትራምፕ አስተያየት በጽሑፍ ምላሽ የሰጡት የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አባስ አራግቺ፣ “በዚህ አይነት ገንዘቦች የሚደሰቱ ወይም የሚያተርፉ አካላት ማስታወስ ያለባቸው፤ መንግሥታት አንዴ ንብረት መውረስን ከተለማመዱ በኋላ የማንም ሀብት ደኅንነቱ የተጠበቀ እንደማይሆን ነው” ብለዋል።

    “ተከትሎ የሚመጣው ቀውስ ያማረ ወይም ሰላማዊ አይሆንም” ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

  6. ኢራን የብሪታኒያ ጦር ሠፈሮች “ሕጋዊ ዒላማ” ናቸው ማለቷን ተከትሎ ዩኬ “ራሷን ለመከላከል ዝግጁ” መሆኗን ገለጸች

    የአሜሪካ ጦር መሣሪያዎች በብሪታኒያ ‘ሮያል ኤር ፎርስ ፌር ፎርድ’ ጦር ሠፈር

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ ጦር መሣሪያዎች በብሪታኒያ ‘ሮያል ኤር ፎርስ ፌር ፎርድ’ ጦር ሠፈር

    ኢራን የዩናይትድ ኪንግደም ጦር ሠፈሮች ለአሜሪካ ጥቃቶች ጥቅም ላይ እየዋሉ ስለሆነ “ሕጋዊ ዒላማ” እንደሆኑ መግለጿን ተከትሎ፤ የብሪታኒያ መንግሥት "ራሱን ለመከላከል 24/7 ዝግጁ" መሆኑን አስታወቀ።

    ዩናይትድ ኪንግደም የአሜሪካ ሠራዊት አባላት እና አውሮፕላኖች ለሚወስዷቸው "የመከላከል" እርምጃዎች የጦር ሠፈሯን እንዲጠቀሙ ፈቅዳለች። ጦር ሠፈሮቹ ኢራን ላይ ለሚደረጉ የማጥቃት እርምጃዎች እንዲያገለግሉ ግን ፍቃድ አልሰጠችም።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ ዩናይትድ ኪንግደም የአሜሪካ ጦርነት “ተባባሪ ነች” ሲል ከስሷል። የኢራን እስላማዊ አብዮት ጠባቂ ዘብ በበኩሉ ለአሜሪካ ጦር ድጋፍ የሚያቀርብ ማንኛውም አገር ለሚከተለው “መዘዝ እና ውጤት ኃላፊነቱን ይወስዳል” ብሏል።

    ሁለቱ አገራት እዚህ ውዝግብ ውስጥ የገቡት፤ አሜሪካ ለ12ተኛ ተከታታይ ምሽት ኢራን ውስጥ በሚገኙ ዒላማዎች ላይ ጥቃት በፈጸመችበት ወቅት ነው።

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ለሚያደርጉት ጦርነት ድጋፍ አልሰጡም በማለት የሚወቅሷቸውን የብሪታንያ መንግሥትን እና የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመርን በተደጋጋሚ ሲተቹ ቆይተዋል። ኢራን ትናንት ሐሙስ ያወጣችው መግለጫ በአንጻሩ ዩናይትድ ኪንግደም የጦርነቱ አጋር እንደሆነች አድርጎ የሚያሳይ ነው።

    አሜሪካ እና እስራኤል የከፈቱት ጦርነት ከተጀመረ ከቀናት በኋላ መጋቢት ውስጥ ዋሽንግተን እንደ በግሎስተርሻየር የሚገኘው ‘ሮያል ኤር ፎርስ ፌር ፎርድ’ እንዲሁም በሕንድ ውቅያኖስ ያለው ዲዬጎ ጋርሲያ ያሉ የብሪታንያ የጦር ሰፈሮችን እንድትጠቀም ፈቃድ ተሰጥቷታል።

    እነዚህ ጦር ሠፈሮች የተፈቀዱት አሜሪካ በፋርስ ባህረ ሰላጤ አገራትን እና በሆርሙዝ ወሽመጥ በሚያልፉ መርከቦችን ለማጥቃት ጥቅም ላይ የሚውሉ የኢራን ወታደራዊ መሠረተ ልማቶችን ዒላማ እንድታደርግ ነበር።

    በፈቃዳቸው ከሥልጣን የተለቀቁትን ጠቅላይ ሚኒስትር የተኩት አንዲ በርንሃም፣ ከአሜሪካ ጋር የተደረገው ስምምነት ስለመራዘሙ የተገለጸላቸው ሲሆን በቀድሞው አስተዳደር የተላለፈውን ይህንን የብሪታኒያ ውሳኔም አልቀየሩም።

    ከኢራን አብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት ያለው ታስኒም የዜና ወኪል ሐሙስ ዕለት የወጣው መግለጫ፤ ከቀናት በፊት የተፈጸመው የአሜሪካ የድብደባ ተልዕኮ የተነሳው ከብሪታኒያው ጦር ሠፈር ‘ሮያል ኤር ፎርስ ፌር ፎርድ’ እንደሆነ ገልጿል።

    የዩናይትድ ኪንግደም መከላከያ ሚኒስትር በዚህ ሳምንት ኢራን ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች አገሪቱ ጦር ሠፈሮች ጥቅም ላይ ውለው እንደሆነ አስተያየት አልሰጠም።

    ለኢራን ዛቻዎች ምላሽ የሰጡት የዩኬ መንግሥት ቃል አቀባይ “ጦር ኃይሎቻችን የዩናይትድ ኪንግደምን ደኅንነት በመሬታችንም ሆነ በውጭ አገራት ከሚፈጸሙ ከማንኛውም ጥቃቶች ለመጠበቅ ዝግጁ ናቸው” ብለዋል። ዩኬ ራሷን ለመከላከል በቀን 24 ሰዓት በሳምንት ሰባት ቀናት ዝግጁ መሆኗንም ጠቅሰዋል።

  7. የነዳጅ ዋጋ ከግንቦት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛ ጭማሪ አሳየ

    ነዳጅ መቅጃ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የሚካሄደው ግጭት መልሶ ከተቀሰቀሰ በኋላ ከግንቦት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የነዳጅ ዋጋ በበርሜል 100 ዶላር ደረሰ።

    የነዳጅ ዋጋ የአሜሪካ ጥቃት በቀጠለባቸው ባለፉት ቀናት በየዕለቱ እየጨመረ ሲሆን የድፍድፍ በርሜል ዋጋ የሚተመንበት ብሬንት ዛሬ ሐሙስ በአምስት በመቶ ጨምሮ 100 ዶላር ደርሷል።

    የአሁኑ ከፍተኛ ጭማሪ የተመዘገበው የየመን ሁቲ ታጣቂዎች በቀይ ባሕር ላይ በሚያልፉ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ ነው። ይህ ጥቃት የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋቱን ተከትሎ ሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ምርቷን ወደ ውጭ የምትልክበትን ወሳኙን የቀይ ባሕር መስመር አደጋ ላይ ጥሏል።

    ከነዳጅ በተጨማሪ የጋዝ ዋጋም ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።

    በዛሬው ዕለት በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ለማቋረጥ የሞከረ አንድ ነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ ፍንዳታ ተከስቶ እሳት ከተነሳ በኋላ ሦስት መርከቦች ጉዟቸውን ማቋረጣቸውን የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ አስታውቋል።

  8. የሳዑዲ እና አሜሪካ የኒውክሌር ስምምነት እንዲፈጸም ሪያድ ለእስራኤል ዕውቅና መስጠት እንዳለባት ትራምፕ ተናገሩ

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና የሳዑዲ አረቢያ አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሰልማን

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    አሜሪካ እና ሳዑዲ አረቢያ የተፈራረሙት ግዙፍ የኒውክሌር ስምምነት ተግባራዊነት የሚወሰነው፤ ሪያድ ለእስራኤል የአገርነት ዕውቅና እንድትሰጥ የሚያደርገውን ‘የአብርሃ አኮርድስ’ ስትቀላቀል እንደሆነ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ።

    ፕሬዝዳንቱ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ “ወታደራዊ ላልሆነ ጥቅም ብቻ የሚውለው… የሲቪል ኒውክሌር ስምምነቱ (ዩራኒየም ማበልጸግ አይኖርም).. ይጽድቃል” ብለዋል።

    የስምምነቱ መጽደቅ “ግን ሳዑዲ አረቢያ እጅጉን የተከበረው እና ስኬታማውን የአብርሃም ስምምነቶችን መቀላቀሏ ላይ የተመሠረተ ነው” ሲሉ ቅድመ ሁኔታውን ይፋ አድርገዋል።

    ትራምፕ ይህንን ያሉት፤ የተፈረመው ስምምነት ቀድሞውኑም አለመረጋጋት ውስጥ ባለው ቀጣና ውስጥ ወደፊት የኒውክሌር መሣሪያ መስፋፋትን ሊያስከትል ይችላል የሚል ወቀሳ ከተሰማ በኋላ ነው።

    ከዚህ ቀደም ሳዑዲ አረቢያ ፍልስጤም አገር ሆና ሳትመሠረት ለእስራኤል ዕውቅና እንደማትሰጥ ገልጻ ነበር።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በአውሮፓውያኑ 2020 እንዲፈረም ያደረጉት አብርሃም አኮርድስ፣ በታሪካዊ ሁኔታ እስራኤል አረብ አገራት ከሆኑት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ባህሬን ጋር ግንኙነት እንዲኖራት ያደረገ ነው።

    ቀጥሎም ሱዳን፣ ሞሮኮ እና ካዛኪስታን ስምምነቱን ተቀላቅለዋል። እስካሁን ድረስ ሳዑዲ ለትራምፕ አስተያየት ምላሽ አልሰጠችም።

    ፕሬዝዳንቱ ይፋ ያደረጉት የአብርሃም አኮርድስን የመቀላቀል ቅድመ ሁኔታ ከሳዑዲ ጋር በተፈረመው ስምምነት ውስጥ በጽሑፍ ተካትቶ፣ ሪያድ ለቅድመ ሁኔታው ተስማምታ አልያም ስምምነቱን ለመቀበል ትገደድ እንደሆነ አልታወቀም። የአሜሪካ እና የሳዑዲ ስምምነት እስካሁን ይፋ አልሆነም።

    እስራኤል በበኩሏ የትራምፕን መግለጫ በበጎ እንደምትቀበለው አስታውቃለች። የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽሕፈት ቤት በኤክስ ገጹ ባወጣው መግለጫ፤ ሳዑዲ አረቢያ ስምምነቱን መቀላቀሏ "በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም ለማስፈን ትልቅ ታሪካዊ እርምጃ ይሆናል" ብሏል።

    የእስራኤል መግለጫ ላይ ስለ ኒውክሌር ስምምነቱ አልተጠቀሰም። የእስራኤል የኢኮኖሚ ሚኒስትር ኒር ባርካት ከዚህ ቀደም፤ ሳዑዲ አረቢያ ለሰላማዊ ዓላማ የሚውል ኒውክሌር ኃይል አገራቸው ጉዳዩን “ማስተዳደር እንደምትችል” ተናግረው ነበር።

    እስራኤል ራሷ የኒውክሌር መሣሪያ እንዳላት በሰፊው የሚታመን ቢሆንም አገሪቱ ግን ማረጋገጫ ሰጥታም ይሁን አተስባብላ አታውቅም።

  9. የአፍሪካ ኅብረት ሁቲዎች በቀይ ባሕር መርከቦች ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት “በአስቸኳይ እንዲያቆሙ” ጠየቀ

    የሁቲ ታጣቂዎች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ፤ የየመኑ አማጺ ሁቲ በቀይ ባሕር መርከቦች ላይ የሚፈጽማቸውን ጥቃቶች "በሙሉ በአስቸኳይ እንዲያቆም" ጠየቁ።

    ሁቲዎች በቀይ ባሕር ሲጓዙ የነበሩ ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ የፈጸሙትን ጥቃት “አደገኛ የውጥረት መባባስ” ሲሉም አውግዘዋል።

    በኢራን የሚደገፉት ሁቲ ጥቃቱን የፈጸመው ሳዑዲ አረቢያ ላይ “የባሕር ጉዞ ማዕቀብ” መጣሉን ካስታወቀ በኋላ ነው። ይህንን እገዳ ጥሰዋል የተባሉ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች በድሮን እና ሚሳዔሎች መመታታቸውን የታጣቂ ቡድኑ ወታደራዊ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሬ ተናግረዋል።

    የአፍሪካ ኅብረት ዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 16/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ድርጊቱን “በጽኑ እንደሚኮንን” አስታውቋል። “እነዚህ እርምጃዎች ለቀጣናው ሰላም እና ደኅንነት ከፍተኛ አንድምታ የሚኖራቸው አደገኛ [የውጥረት] መባባሶች ናቸው” ብሏል።

    መርከቦቿ ለተመቱባት ሳዑዲ አረቢያ አጋርነቱን የገለጸው አፍሪካ ኅብረት፤ ለአገሪቱ “ደኅንነት፣ ሉዓላዊነት እና መረጋጋት የማይናወጥ ድጋፍ” እንዳለውም አስታውቋል።

    የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ፣ ይህ አይነቱ ድርጊት “ለዓለም አቀፍ የባሕር ጉዞ ደኅንነት እንዲሁም ከዓለም ስትራቴጂካዊ የውሃ መስመሮች አንዱ” ለሆነው ቀይ ባሕር “መረጋጋት ከፍተኛ ስጋት” መሆኑን በአጽንኦት አንስተዋል።

    “ነጻ የመርከብ ጉዞን ለማደናቀፍ የሚደረግ ማንኛውም ሙከራንም” አውግዘዋል። በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት የባሕር ጉዞ ነፃነት ዝውውር እና የንግድ መርከቦች ደኅንነት እና ጥበቃ ሙሉ በሙሉ መከበር እንዳለበትም በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።

    ሁቲዎችም “ንግድ መርከቦች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት በሙሉ በአስቸኳይ እንዲያቆሙ” እንዲሁም “ውጥረቱን የበለጠ ሊያባብሱ የሚችሉ የትኛውም እርምጃዎችን ከመውሰድ እንዲቆጠቡ” ሊቀ መንበሩ ጥሪ አቅርበዋል። “የባሕር ጉዞ የሚመራባቸው ዓለም አቀፍ ሕጎችን ሙሉ በሙሉ እንዲያከብሩም” ጠይቀዋል።

  10. ኢራን በሲአይኤ ተቋማት ላይ የፈጸመችው ጥቃት የሩሲያ እጅ አለበት የሚል ጥርጣሬን ፈጠረ

    የኢራን ድሮኖች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የኢራን ድሮኖች በባሕረ ሰላጤው በሚገኙ የሲአይኤ ተቋማት ላይ ጥቃት ከማድረሳቸው ጋር በተያያዘ ሩሲያ መረጃ በመስጠት ወይም የተሻሻለ የድሮን ቴክኖሎጂ በማቅረብ ተሳትፎ አድርጋ ስለመሆኑ ምርመራ መደረግ እንዳለበት የአሜሪካ የደኅንነት ባልደረቦች ለሮይተርስ ተናገሩ።

    ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አራት የአሜሪካ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ባልደረቦች ለዜና ወኪሉ እንደተናገሩት የኢራን ጥቃት ላይ የሩሲያ ተሳትፎ መኖሩ ላይ ምርመራ መደረግ ይኖርበታል።

    ስማቸው ሳይጠቀስ ለሮይተርስ አስተየየታቸውን የሰጡት ምንጮች ኢራን በሲአይኤ ተቋማት ላይ ለፈጸመችው ጥቃት ሩሲያ እጇ ስለመኖሩ ድምዳሜ ላይ አልተደረሰም ብለዋል።

    ነገር ግን የጥቃቱ ‘ዒላማውን የጠበቀ መሆን እና ውጤታማነቱ’ እንዲሁም ሩሲያ ለኢራን የምትሰጠው ሰፊ የቴክኒክ ድጋፍ ለጥርጣሬው በማስረጃት ግብዓት የመሆን ዕድል አለው ተብለዋል።

    ሮይተርስ እና ሌሎች መገናኛ ብዙኃን የአሜሪካ ባለሥልጣናት ሩሲያ ኢራን በባሕረ ሰላጤው ላይ በምትፈጽማቸው ጥቃቶች ላይ የቴክኒክ ድጋፍ እንደምታደርግ እንደሚያውቁ ዘግበዋል።

    መጋቢት ወር በባሕረ ሰላጤው የሚገኙ ሁለት የሲአይኤ ተቋማት ላይ ጥቃት መድረሱን ሮይተርስ ዘግቧል።

    አንዱ ተቋም በሪያድ ከሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ አቅራቢያ ያለ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በምሥራቃዊ ኢራቅ ያለ ነው።

    ሮይተርስ ያነጋገራቸው ምንጮች ሌሎች የሲአይኤ ተቋማትም ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ገልጸው ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

  11. በስደተኞች ጥቃት ምክንያት ደቡብ አፍሪካ በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ተከሰሰች

    ዱላ እና ጋሻ የያዙ ሰልፈኞች

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ስደተኞች ከደቡብ አፍሪካ እንዲወጡ የሚጠይቁ ሰልፎች በተከታታይ እየተካሄዱ ነው

    ሁለት ጋናውያን በደቡብ አፍሪካ ውስጥ በውጭ አገር ዜጎች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት በሰብአዊነት ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች ጋር የሚስተካከል ነው በማለት የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ምርመራ እንዲያደርግ ጥያቄ አቀረቡ።

    ክሱን ያቀረቡት የቀድሞው የጋና መንግሥት ቃል አቀባይ የሆኑት ፓልግሬቭ ቦአካይ-ዳንኬህ እና የፀረ ሽብርተኝነት እና የደኅንነት ተንታኝ የሆኑት ኢማኑኤል ኮቲን ናቸው።

    ሮይተርስ የዜና ወኪል የተመለከተው እና ከ10 ቀናት በፊት ለፍርድ ቤቱ የቀረበው ክስ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ “መጠነ ሰፊ እና የተቀናጀ ቅርጽ ያለው” ጥቃት በስደተኞች ላይ እንደሚፈጸም ያመለክታል።

    በተጨማሪም የፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ መንግሥት ጥቃቱን ለመከላከል እና የወንጀሉን ፈጻሚዎች ለመቅጣት አልቻለም ሲል ይወቅሳል።

    የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የቀረበውን ክስ አጋጣሚውን ለመጠቀም የታሰበ እንዲሁም ሕጋዊ ቅድመ ሁኔታዎችን እና ፍርድ ቤቱ እርምጃ እንዲወስድ የሚያስችለውን ሁኔታ የማያሟላ በማለት አጣጥሎታል።

    ጋና በደቡብ አፍሪካ የሚካሄደውን የፀረ ስደተኞች ተቃውሞ ተከትሎ ዜጎቻቸውን ካስወጡ አገራት መካከል አንዷ ናት። በዚህ ጥቃትም አንድ ዜጋዋ ተገድሏል በማለት የምትከስ ሲሆን፣ የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናት ግን ግድያውን ያስተባብላሉ።

    በዚህም የተነሳ ባለፉት ወራት በጋና እና በደቡብ አፍሪካ መካከል የተጋጋለ ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ተፈጥሯል።

  12. አሜሪካ የጦር መሣሪያ ለዩክሬን መስጠቷን ሩሲያ ተቃወመች

    የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ከአሜሪካ አቻቸው ማርኮ ሩቢዮ ጋር

    የፎቶው ባለመብት, AP

    የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሜሪካ ለዩክሬን የጦር መሣሪያ መስጠቷ “ተቀባይነት የለውም” ሲሉ ተቃውሟቸውን ገለጹ።

    የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ከአሜሪካ አቻቸው ማርኮ ሩቢዮ ጋር በፊሊፒንስ ዋና ከተማ ማኒላ ሐሙስ ዕለት ተገናኝተው ተወያይተዋል።

    ሰርጌይ ላቭሮቭ “በኪየቭ ለሚገኘው መንግሥት የጦር መሣሪያ ማቅረብ መቀጠል ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል” ሲል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ ላይ ጠቅሷል።

    እንደ ሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ከሆነ ላቭሮቭ ሩሲያ በዩክሬን ግጭት ዙሪያ ለፖለቲካዊ እና ለዲፕሎማሲያዊ መፍትሔዎች ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።

    ላቭሮቭ በማኒላ እየተካሄደ በሚገኘው የእስያ አገራት ጉባዔ ላይ ባደረጉት የጎንዮሽ ውይይት “በሩሲያ ላይ ‘ስትራቴጂያዊ ሽንፈት’ እንዲደርስ ዒላማ እያደረጉ ያሉ የአውሮፓ አገራትን አፍራሽ ሚና” ኮንነዋል።

    የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ ሁለቱ ሚኒስትሮች “በአገራቱ መካከል ስላለው ግንኙነት እና የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ማብቃት አስፈላጊነት ላይ ተነጋግረዋል” ብለዋል።

    ከስብሰባው በኋላ ማርኮ ሩቢዮ በሰጡት መግለጫ አሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “የማይረባ ጦርነት” እንደሆነ ያስባሉ፤ እንዲሁም አሜሪካ በዩክሬን ከስምምነት ለመድረስ ዕድል በኖረ ጊዜ “እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ናት” ማለታቸውን ጋርዲያን ዘግቧል።

    ረቡዕ ዕለት ማርኮ ሩቢዮ ለጋዜጠኞች በዩክሬን የሚካሄደው ጦርነት “አሜሪካ እና ሩሲያ ሊስማሙ የሚችሉበትን ነጥብ በበርካታ መንገዶች ጎድቷል” ብለዋል።

  13. በሜታ ላይ ማኅበራዊ ሚዲያዎቹ ሱስ ሆነውብኛል ሲል ክስ የመሠረተው ታዳጊ ክሱን አቋረጠ

    ሁለት ሴቶች ሞባይላቸውን ሲመለከቱ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ወላጆች እና ታዳጊዎች በተደጋጋሚ ማኅበራዊ ሚዲያ አሉታዊ ተጽዕኖ እነዳለው በመጥቀስ ይከራከራሉ

    እንደ ኢንስታግራም ባሉ የማኅበራዊ መድረኮች ሱስ በመያዙ ጉዳት እንደደረሰበት በመግለጽ ሜታ ላይ ክስ የመሠረተው የፍሎሪዳ ታዳጊ ክሱን አቋርጧል።

    የ15 ዓመቱ ከሳሽ አርኬኤስ በሚል ምህጻረ ቃል የሚታወቅ ሲሆን በቲክቶክ፣ በስናፕቻት እና በዩቲዩብ ላይ ተመሳሳይ ክሶችን መሥርቷል።

    የታዳጊው ክሶች በሙሉ ለሕፃናት ጎጂ የሆኑ ሱስ የሚያስይዙ የማኅበራዊ መድረኮችን በመፍጠር ላይ ያተኮሩ ናቸው።

    የአርኬሲ ክሶች ሜታ እና ዩቲዩብ ከዚህ በፊት በተመሠረቱባቸው የሎስ አንጀለስ ችሎት በሚቀጥለው ሳምንት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቅ ነበር።

    የሜታ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ "ክሱ ውሃ አይቋጥርም፤ እናም ይህ ውጤትም መሠረተ ቢስ ክሶችን ከመከላከል ወደኋላ እንደማንል ግልጽ ያደርገዋል" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

    የአርኬሲ ጠበቆች ኤሚሊ ጄፍኮት እና ራሁል ራቪፑዲ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ታዳጊው ከሳሽ "በዚህ ሂደት ውስጥ የማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎችን ተጠያቂ ለማድረግ እና እንደ እርሱ ያሉ ታዳጊዎችን ለመጠበቅ ለውጦችን እንዲያደርጉ እየሞከረ ነው" ብለዋል።

    “ይህንን ነው ያደረገው” ሲሉ አክለዋል።

    ጠበቆቹ ለሳምንታት የተራዘመውን የፍርድ ቤት ቀጠሮ ጠቅሰው ስጋታቸውን ገልጸው የነበረ ሲሆን፣ አርኬሲ "ይህንን ምዕራፍ ለመዝጋት እና በራሱ በማተኮር መደበኛ ሕይወቱን ለመቀጠል ስለሚፈልግ የሕክምና ድጋፍ ለማግኘት ዝግጁ ነው" ብለዋል።

    የሜታ ቃል አቀባይ ክሱ ውድቅ እንዲደረግ ምንም ዓይነት ክፍያ እንዳልከፈሉ ተናግረዋል።

    አርኬሲ በማኅበራዊ ሚዲያዎቹ ላይ ያለ ገደብ እየቀያየሩ መመልከት መቻል እና ያለ ፈቃድ በገጽ ላይ የሚመጡ ይዘቶችን በመጥቀስ ሁለቱም በተከታታይ እና ወዲያው ወዲያው ለተጠቃሚዎች አዲስ ይዘት እንዲመለከቱ ስለሚያደርጉ ሱስ እንዲሆኑ ያደርጋል ብሏል።

    ይህ ጭንቀት እና እንቅልፍ ማጣት እንዲሁም ሌሎች ችግሮችን እንዳስከተለበት በመግለጽ ተከራክሯል።

    ሜታ እና ዩቲዩብ የችሎት ሂደቱ ሲጀመር ከአንዲት ወጣት ሴት ተመሳሳይ ክሶች ቀርቦባቸው ነበር።

  14. የቀድሞው የቬንዙዌላ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ክስ በሚቀጥለው ዓመት እንደሚታይ ተነገረ

    በአሜሪካ ከሥልጣናቸው ተነስተው በኒውዮርክ የታሰሩት የቀድሞው የቬንዙዌላ ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በአሜሪካ ከሥልጣናቸው ተነስተው በኒው ዮርክ የታሰሩት የቀድሞው የቬንዙዌላ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ እና ባለቤታቸው ሲሊያ ፍሎሬስ ክሳቸው በሚቀጥለው ዓመት ሰኔ ወር መታየት እንደሚጀምር ተገለጸ።

    የአሜሪካ ወታደሮች ጥር ላይ በሌሊት በፈጸሙት ድንገተኛ ጥቃት ማዱሮን እና ባለቤታቸውን በቬንዙዌላ ዋና ከተማ ካራካስ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በቁጥጥር ስር አውለው ወደ አሜሪካ ወስደዋቸዋል።

    የቀድሞው የቬንዙዌላ ፕሬዝዳንት እና ባለቤታቸው የጦር መሳሪያ እና የአደንዛዥ ዕፅ ወንጀል በኒው ዮርክ ክስ የተመሠረተባቸው ቢሆንም እርሳቸው ግን ውንጀላውን ክደዋል።

    ረቡዕ ዕለት ክሱን የተመለከቱት ዳኛ አልቪን ሄለርስቴይን የሁለቱንም ወገኖች የቅድመ ችሎት አቤቱታ ለመስማት በሚወጥለው ዓመት ኅዳር አጋማሽ ላይ ቀጠሮ ሰጥተዋል።

    የማዱሮ ጠበቃ ባሪ ፖላክ ደንበኛቸው የአገር መሪዎችን ያለ መከሰስ መብት በሚሰጠው የሉዓላዊነት ዋስትናን በመግለጽ በችሎት እንደሚከራከሩ ገልጸዋል።

    ማዱሮ ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት እርሳቸውን ለማየት የሚፈልጉ ግለሰቦች በፍርድ ቤቱ አካባቢ ለሰዓታት ተሰልፈው የነበረ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ በታዳሚዎች ተሞልቶ ነበር ተብሏል።

    ችሎቱ ከመጀመሩ በፊት፣ የፍርድ ቤቱ ባልደረባ በችሎት የተገኘው ታዳሚ ከመቀመጫቸው እንዳይነሱ አስጠንቅቀው "ምንም ነገር መናገር እንደማይችሉ" አሳስበዋል።

    የፍርድ ቤቱን ሥነ ምግባር የሚጥስ ካለ “የሕግ ቅጣት እንደሚጠብቀውም” ጨምረው ተናግረዋል።

    ይህንንም ተከትሎ በችሎቱ የተገኙ ታዳሚዎች ማዱሮ እና ባለቤታቸው ወደ ችሎቱ ሲገቡ በዝምታ ሂደቱን ተከታትለዋል።

  15. አሜሪካ በኢራን ላይ ተጨማሪ ድብደባዎችን ስታካሂድ ሁቲዎች የነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተናገሩ

    ባብል መንደብ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, በየመን የሚገኙት የሁቲ ታጣቂዎች ለባብል መንደብ በቅርብ ርቀት ላይ ይገኛሉ

    አሜሪካ ለ12 ተከታታይ ሌሊቶች ኢራን ላይ ድብደባ ስትፈጽም የየመን ሁቲዎች ሁለት የሳዑዲ የነዳጅ ጫኝ መርከቦችን ማጥቃታቸውን ተናገሩ።

    የኢራን መገናኛ ብዙኃን ረቡዕ ዕለት አሜሪካ በፈጸመችው ጥቃት ሁለት ሰዎች መገደላቸውን እንዲሁም በሆርሙዝ ወሽመጥ ፈንጂ በተቀበረበት የውሃ ክፍል ላይ የሚያልፍ ነዳጅ ጫኝ መርከብ በእሳት መያያዙን ዘግበዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የሚያልፉ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸሟን ከቀጠለች ድልድዮቿን ወይንም የኃይል ማመንጫዎቿን እንደሚያወድሙ ዝተው ሁቲዎች የቀይ ባሕርን የሚዘጉ ከሆነ ደግሞ “እርምጃ እንደሚወስዱ” አስጠንቅቀዋል።

    ሁቲዎች ያሉት እውነት መሆኑ ከተረጋገጠ በኢራን የሚደገፈው ቡድኑ በሳዑዲ አረቢያ ላይ “የባሕር ላይ እንቅስቃሴ ገደብ” ከጣለ በኋላ የተፈጸመ የመጀመርያው ጥቃት ነው የሚሆነው።

    በሁቲዎች ጥቃት የተፈጸመባቸው መርከቦቹ ስም ኢንሴሊያ እና ላይላ እንደሚባል ቢጠቅሱም ላይላ ላይ የተፈጸመው ጥቃት አልተረጋገጠም።

    የቡድኑ ወታደራዊ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሬ መርከቦቹ የተጣለባቸውን እገዳ በመጣሳቸው በድሮን እና በሚሳኤሎች ጥቃት መፈጸማቸውን አስታውቀዋል።

    የሳዑዲ ፕሬስ ኤጀንሲ በበኩሉ ሐሙስ ዕለት ኢንሴሊያ የተባለችው መርከብ “በቀይ ባሕር ላይ እየቀዘፈች ሳለ” ጥቃት እንደተፈጸመባት እና እሳት ተነስቶ እንደነበር ዘግቧል።

    በአገሪቱ ትራንስፖርት ባለሥልጣን መስሪያ ቤት ውስጥ ያሉ ስማቸው ያልተጠቀሱ ምንጭ ጥቃቱ ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ ነው ማለታቸው ተጠቅሷል።

    የመርከቧ ሁሉም ሠራተኞች ደህንነታቸው የተጠበቀ መሆኑን ጨምሮ የዜና ኤጀንሲው በዘገባው ላይ አስታውቋል።

    የዩኬ ባሕር ትራንስፖርት እና ንግድ ባለሥልጣን በበኩሉ የሳዑዲ ነዳጅ ጫኝ መርከብን “ምንነቱ ያልታወቀ ተወንጫፊ” እንደመታት አስታውቋል።

    ሰኞ ዕለት የሁቲ ታጣቂዎች “የባሕር ላይ ትራንስፖርት እገዳ” የጣሉ ሲሆን የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልናት ደግሞ በቀይ ባሕር ደቡባዊ መግቢያ ላይ የሚገኘውን ባብ አል ማንዳብን ለሳዑዲ መርከቦች ዝግ ሊያደርጉ መሆኑን ዘግበዋል።

    አሜሪካ እና እስራኤል ቴህራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ በኋላ የሆርሙዝ ወሽመጥ ሙሉ በሙሉ በመዘጋቱ ቀይ ባሕር ቁልፍ የነዳጅ መተላለፊያ በመሆን እያገለገለ ነው።

    የሁቲ አማፂያን በቀይ ባሕር ላይ የሚደረገውን የመርከቦች እንቅስቃሴ ማወካቸውን ተከትሎ ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ መታየት ጀምሯል።

    ሰኞ ዕለት እገዳው ከተጣለ ጊዜ አንስቶ ዘጠኝ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ወደ የመን ሲቃረቡ ወደ መጡበት ለመመለስ ተገድደዋል።

    ቃል አቀባዩ ሳሬ “በግምት አስር መርከቦች እንዲያፈገፍጉ እና እንዲመለሱ ማድረግ ችለናል” ሲሉ ተናግረዋል።

  16. አሜሪካ በፈጸመቸቻው ጥቃቶች 53 ኢራናውያን መገደላቸውን የአገሪቱ ባለሥልጣን አስታወቁ

    ጉዳት የደረሰበት ድልድይ

    የፎቶው ባለመብት, Tasnim

    የምስሉ መግለጫ, አሜሪካ በኢራን ላይ በምትፈጽማቸው ጥቃቶች መሠረተ ልማቶችም ዒላማ ሆነዋል

    አሜሪካ በኢራን ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት መልሳ በመጀመር 11ኛ ቀኑን በያዛበት በአሁኑ ጊዜ ኢራን ውስጥ 53 ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ የጤና ሚኒስትር አስታወቁ።

    የጤና ሚኒስትሩ ሆሴይን ኬርማንፑር የአሜሪካ ጥቃት በአገራቸው ዜጎች ላይ ያደረሰውን ጉዳት በተመለከተ በኤክስ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ አስፍረዋል።

    ሚኒስትሩ ተገደሉ ካሏቸው ሰዎች በተጨማሪ 592 ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ያመለከቱ ሲሆን፣ ነገር ግን በጥቃቶቹ የተገደሉት እና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ወታደሮች ወይም ሲቪሎች መሆናቸውን አልጠቀሱም።

    የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ባለፈው የካቲት ወር አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር ጦርነት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ቢያንስ 18 የአሜሪካ ወታደራዊ ወታደሮች ተገድለዋል።

    ከቀናት በፊት የአሜሪካንን ጥቃት ተከትሎ ኢራን በዮርዳኖስ በሚገኝ የአሜሪካ ጦር ሰፈር ላይ የሚሳዔል ጥቃት መፈጸሟን አሜሪካ አረጋግጣለች። ሞዋፍቃት አል-ሱልቲ በተባለው ጦር ሰፈር ላይ በተፈጸመው በዚህ ጥቃትም ሦስት ወታደሮቿ ተገድለውባታል።

    አራተኛው ወታደሯ ደግሞ ኢራቅ ኤርቢል ውስጥ አንድ ጥቃት ፈጻሚ የኢራን ድሮን እንዲፈነዳ በተደረገበት ጊዜ ሕይወቱ ማለፉ ተገልጿል።

    አሜሪካ በኢራን ላይ ለምትፈጽማቸው ጥቃቶች ኢራን በዮርዳኖስ፣ በኩዌት እና በባህሬን ውስጥ በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች እና ወታደራዊ ተቋማት ላይ የአጸፋ እርምጃ እየወሰደች ነው።

  17. ዱባይ በጦርነቱ የሸሹ ጎብኚዎችን ለመሳብ ቅናሽ እና ማበረታቻ ልትሰጥ ነው

    ባደ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በጦርነቱ ምክንያት የዱባይ ቱሪስት መዳረሻዎች ባዶ ሆነዋል

    የተበባሩት አረብ ኤምሬትስ ታዋቂዋ የቱሪስት ከተማ ዱባይ በጦርነት ምክንያት የተዳከመውን የቱሪስት ፍሰት ለማነቃቃት ለወራት የሚቆይ ልዩ ቅናሽ በመስጠት ጎብኚዎችን ልታበረታታ መሆኗን አስታወቀች።

    ቤተሰቦቻቸውን እና ጓደኞቻቸውን ወደ ዱባይ ለጉብኝት የሚጋብዙ የከተመዋ ነዋሪዎች ከ800 ዶላር በላይ ቅናሽ እና ልዩ መስተንግዶ እንደሚቀርብላቸው የዱባይ የመገናኛ ብዙኃን ጽህፈት ቤት ዛሬ ረቡዕ አስታውቋል።

    ይህ አስከ መጪው ዓመት ጥቅምት ድረስ የሚቆየው ማበረታቻ የተዘጋጀው በባሕረ ሰላጤው እየተካሄደ ያለው ጦርነት በግዛቲቱ የቱሪዝም ዘርፍ ላይ ያስከተለውን ጫና እና ጉዳት ለመቀነስ ነው።

    የዱባይ አስተዳደር በድረገጹ ላይ እንዳመለከተው ከአሁን ጀምሮ አስከ ጥቅምት ወር መጨረሻ ድረስ ቤተሰቦቻቸውን እና ጓደኞቻቸውን ለጉብኝት የሚጋብዙ ነዋሪዎች የሚያርፉበት ሆቴል፣ የምግብ እና የጉብኝት ቦታዎች ትኬቶችን ጨምሮ የተለያዩ ጥቅማጥቆሞችን ያገኛሉ።

    በመካከለኛው ምሥራቅ ዋነኛዋ የቱሪስት መዳረሻ የሆነችው አንዷ በየዓመቱ 19.5 ሚሊዮን ጎብኚዎችን ስታስተናግድ ቆይታለች።

    ነገር ግን አሜሪካ እና አስራኤል በኢራን ላይ ባካሄዱት ከአንድ ወር በላይ በዘለቀ ጦርነት የቱሪስት ፍሰቷ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል።

    በጦርነቱ ወቅት ኢራን የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን ዒላማ ያደረገች ሲሆን፣ ሆቴሎች እና ታላላቅ ተቋማቷ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል።

    በዚህም የተነሳ በወሳኙ የጎብኚዎች ጊዜ በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት በርካታ ቱሪስቶች አገሪቱን ለቅቀው መውጣታቸው ተዘግቧል።

    ሚያዝያ ላይ የተኩስ አቁም ከተደረገ በኋላ የተወሰኑ ጎብኚዎች ወደ አገሪቱ ቢገቡም የቀደመው የቱሪስቶች ፍሰት አልተመለሰም። በዚህም የተነሳ የዱባይ መንግሥት በጦነርቱ ጫና የደረሰባቸውን የንግድ ተቋማትን ለማገዝ የ400 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አቅርቧል።

  18. የየመን ሁቲዎች ዛሬም በቀይ ባሕር ላይ መርከቦች እንዳይተላለፉ አገዱ

    የጭነት መርከብ በቀይ ባሕር ላይ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በቀይ ባሕር ግዙፍ መርከቦች ነዳጅ እና ሌሎች ጭነቶችን ይዘው የሚተላለፉበት ወሳኝ መስመር ነው

    የየመን ሁቲዎች በሳዑዲ አረቢያ ላይ የባሕር እንቅስቃሴ ገደብ ከጣሉ በኋላ ተጨማሪ መርከቦች በቀይ ባሕር በኩል እንዳያልፉ መከልከላቸው ተዘገበ።

    ማክሰኞ ዕለት ከሳዑዲ ወደብ የተነሱ ሦስት ግዙፍ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው አቅጣጫቸውን የቀየሩ ሲሆን፣ ዛሬ ረቡዕ ደግሞ አራት የሳዑዲን ነዳጅ የጫኑ መርከቦች በደቡባዊ ቀይ ባሕር በኩል ማለፍ በመከልከላቸው ወደ ኋላ መመለሳቸው ተዘግቧል።

    ከአሜሪካ ጋር ጦርነት ውስጥ የገባችው የኢራን አጋር የሆኑት እና የየመን የባሕር ዳርቻ የሚቆጣጠሩት ሁቲዎች ሰኞ ዕለት ወደ ሳዑዲ የሚሄዱ እና ከሳዑዲ የሚነሱ መርከቦች በቀይ ባሕር በኩል ወደ ባብ ኤል መንደብ ማለፍ እንደማይችሉ አስጠንቅቀዋል።

    ዛሬ አቅጣጫቸውን እንዲቀይሩ ከተገደዱት መርከቦች መካከል ሁለቱ ወደ ሰሜን በማቅናት በሱዩዝ ካናል በኩል ጉዟቸውን እንዳደረጉ ተዘግቧል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የአውሮፓ ባሕር ኃይል ከአሜሪካ፣ ከእስራኤል እና ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ግንኙነት ያላቸው መርከቦች ለጊዜው በቀይ ባሕር በኩል ጉዞ እንዳያደርጉ አስጠንቅቋል።

    ለዚህም ምክንያቱ ከአገራቱ ጋር የሚያያዙ መርከቦች በሁቲ ታጣቂዎች ጥቃት ሊፈጸምባቸው የሚችልበት ከፍተኛ ዕድል ስላላቸው መሆኑን በመጥቀስ በጉዞ ላይ ያሉም ከሆነ አቅጣጫቸውን እንዲቀይሩ መክሯል።

    በቀይ ባሕር የመርከቦች እንቅስቃሴ ላይ የተፈጠረው ስጋት በሆርሙዝ ሰርጥ ላይ ለወራት ካለው ቀውስ ጋር ተደማምሮ በዓለም የነዳጅ አቅርቦት ላይ ጫና ስለሚፈጥር የዋጋ ጭማሪ ማስከተሉ እንደማይቀር እየተነገረ ነው።

  19. የአሜሪካ እና የኢራን ጥቃት ሲቀጥል የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳየ

    እየፈጸመችው ያለው ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    አሜሪካ ለተከታታይ ቀናት በኢራን ላይ እየፈጸመችው ያለውን ጥቃት ተከትሎ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት እና ሆርሙዝ ወሽመጥ የኢራን የአጸፋ ጥቃት ዒላማ ሲሆኑ የነዳጅ ዋጋም ከፍተኛ ጭማሪ አሳየ።

    በተለይ ዮርዳኖስ ባለፉት ተከታታይ ቀናት በኢራን ሚሳዔሎች ተከታታይ ጥቃቶች የተፈጸሙባት ሲሆን፣ ሚሳዔሎቹን ለማክሸፍ በምታደርገው ጥረት ተወጥራለች።

    የእስራኤል አጎራባች በሆነችው ዮርዳኖስ ላይ በዛሬው ዕለት ስድስት የኢራን ሚሳዔሎች እንደተተኮሱባት እና የአገሪቱ ጦር ሠራዊት አራቱን ማክሸፉን አስታውቋል። ሁለቱ ደግሞ ሰው በማይኖርባቸው ራቅ ያሉ ስፍራዎች ላይ መውደቃቸውን ፔትራ የተባለው የዜና ወኪል ዘግቧል።

    የእስራኤል ኤይላት ከተማ ነዋሪዎች የቀረጹት እና በቀይ ባሕር ዳርቻ ላይ ከምትገኘው አቃባ ከተማ ላይ የሚነሳ ጭስ ወደ ሰማይ ሲወጣ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች መታየታቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል።

    እስራኤል በዮርዳኖስ ላይ የተፈጸሙት ጥቃቶች የፈጠሩት ጭስ ከድንበሯ ባሻገር መታየታቸው ስጋት የፈጠረባቸው የእስራኤል ባለሥልጣናት የኢራን ጥቃት ወደ ግዛታቸው ሊሸጋገር እንደሚችል እያስጠነቀቁ ነው።

    ዮርዳኖስ የአሜሪካ ጦር ሠራዊት አባላት እና አውሮፕላኖች በግዛቷ ውስጥ እንዲሰፍሩ በመፍቀዷ በተደጋጋሚ የኢራን ጥቃት ዒላማ ሆናለች። በተጨማሪም ኩዌት እና ባህሬን ባለፉት ቀናት የኢራን ጥቃት ደርሶባቸዋል።

    በፋርስ ባሕረ ሰላጤው አካባቢ የሚደረገው የኢራን እና የአሜሪካ ጦርነት ዳግም ከተቀሰቀሰ በኋላ የሆርሙዝ ወሽመጥ ደኅንነት አደጋ ላይ በመውደቁ መርከቦች ስጋት ተደቅኖባቸዋል።

    ባለፉት ሳምንትታት በርካታ መርከቦች በተወንጫፊዎች በመመታታቸው የነዳጅ ጫኝ መርከቦች እንቅስቃሴ በከፍተኛ መጠን ቀንሷል።

    በዚህም ሳቢያ በጦርነቱ መቆም ከፍተኛ ቅናሽ አሳይቶ የነበረው የነዳጅ ዋጋ እያሻቀበ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከሰኔ ወር መጀመሪያ ወዲህ ከፍተኛ የሆነው ደረጃ ላይ ደርሷል።

    በዛሬው የብሬንት የነዳጅ ገበያ ተመን መሠረት የአንድ በርሜል ዋጋ ወደ 94 ዶላር በመድረስ ከአንድ ወር በላይ በሆነ ጊዜ ውስጥ ዋጋው ከፍተኛ መጠን ላይ ደርሷል።

    ኢራን በአሜሪካ በሚፈጸምባት ጥቃት ምክንያት በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት እና በሆርሙዝ ወሽመጥ መመሪያዋን በሚጥሱ መርከቦች ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት አጠናክራለች።

    በዚህም የተነሳ ለመርከቦች ያወጣችውን “መመሪያ አላከበሩም” ያላቻቸውን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ሊያቋርጡ የነበሩ ሁለት መርከቦች ማስቆሟን እና ጥቃት መፈጸሟን አስታውቃለች።

  20. ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን መቆጣጠሯ “አደገኛ አካሄድ” መሆኑን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናገሩ

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ከኢራን ጋር የተፈጠረውን ቀውስ ለመግታት በሚል ዋሽንግተን ለድርድር “አሁንም ዝግጁ ብትሆንም” ቴህራን ግን “ድርድርን በቁም ነገር እንደማትወስድ” ገለጹ።

    ሩቢዮ ይህንን የተናገሩት ከደቡብ ምሥራቅ እስያ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ሲሆን፤ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን መቆጣጠሯ “አደገኛ አካሄድ ነው” ሲሉም ገልጸዋል።

    ከፍተኛ የኢራን ባለሥልጣን ሰኞ ዕለት ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት፤ ቴህራን ለ10 ቀናት የተኩስ አቁም እንዲደረግ ከአሸማጋዮች ጥያቄ ቀርቦላታል።

    የኢራን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ትናንት ማክሰኞ ወደ ፓኪስታን ተጉዘው ከአገሪቱ ወታደራዊ አዣዥ ጋር ተወያይተዋል።

    ሩቢዮ ከደቡብ ምሥራቅ እስያ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ባደረጉት ውይይት፤ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን መቆጣጠሯ “አደገኛ አካሄድ” መሆኑን ጠቅሰው የዚህም ዳፋ ከመካከለኛው ምሥራቅ ይሻገራል ብለዋል።

    አሜሪካ በኢራን ላይ የምትፈጽመው ጥቃት 11ኛ ቀኑን ይዟል።

    የአሜሪካ ሠራዊት ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) እንዳለው በኢራን ላይ እየደረሰ ያለው ተከታታይ ጥቃት ዓላማው በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ “ለንግድ መርከቦች አስጊ የሆነ አቅሟን ለማዳከም” ነው።

    ሩቢዮ “ዓለም አቀፍ የውሃ መተላለፊያን አንድ አገር የሚቆጣጠር፣ ከመርከቦች ክፍያ የሚጠይቅ እና የማይከፍሉትን ዒላማ የሚያደርግበት አካሄድ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚኖር ከሆነ አደገኛ አካሄድ ይፈጠራል” ብለዋል።

    “አደገኛ” ያሉት አካሄድ ቀጣናውን ጨምሮ በሌሎች የዓለም ክፍሎችም “ሊደገም” እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል።

    ኢራን እና አሜሪካ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ደርሰው የነበረ ቢሆንም በሆርሙዝ ወሽመጥ አስተዳደር ጉዳይ ዳግመኛ ወደ ውጊያ ተመልሰዋል።

    ኢራን አሜሪካ እየፈጸመችባት ላለው ጥቃት በምላሹ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ የጦር ሰፈሮቿን ዒላማ አድርጋ የአጸፋ እርምጃ እየወሰደች ነው።

    ኢራን በተደጋጋሚ አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ አስተዳደር ላይ መብት እንደሌላት ገልጻለች።

    ቴህራን “ከ30 በላይ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት ፈጽማለች” ሲል የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ከስሷል።

    ማርኮ ሩቢዮ ባደረጉት ንግግር “ጉዳዩ ቀላል ነው። ኢራን ሕጋዊ መነሻ ሳይኖራት የሆርሙዝ ወሽመጥን የመቆጣጠር መብትን እየጠየቀች ነው” ብለዋል።